Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዕይታ) የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እና የሰርከስ ጅምናስቲክ ባለሙያዎች አንድ የሚያመሳስላቸው ድንቅ ጠባይ አለ፤ ሁለቱም አየር ላይ ይገለበጣሉ፣ ግን መሬት ላይ ሲያርፉ እግራቸው አይሰበርም። ልዩነቱ የሰርከስ ባለሙያው ሲገለበጥ የራሱን ህይወት አደጋ ላይ ሲጥል፣ ፖለቲከኛው ግን ሲገለበጥ የህዝብን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉ ነው።
ዛሬ በኒውዮርክ ከተማ፣ በ81ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ (UNGA) ደጃፍ ላይ የታየው ትዕይንት ይህንኑ የፖለቲካችንን የሰርከስ ትርዒት በሚገባ ያሳያል። አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እና የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከአስር ዓመታት በኋላ ተገናኝተው ተቃቅፈዋል። አቶ ጌታቸውም በምስሉ ላይ እንደሚታየው፣ ጥርሳቸው እስከ መንጋጋቸው እስኪታይ በደስታ ተሞልተው፣ "ወንድሜን ዶ/ር ቴድሮስን ከአስር ዓመት ገደማ በኋላ በኒውዮርክ ማግኘቴ ትልቅ ደስታ ነው" ብለው ጻፉልን።

አስር ዓመት! ለፖለቲከኛ አስር ዓመት ማለት አንዲት የቡና እረፍት ያህል አጭር ናት። ለኢትዮጵያ ምስኪን እናቶች ግን አስር ዓመት ማለት... አያሌ የጦርነት፣ የምጥ፣ የረሃብ እና የስደት ዘመን ነው። ምስኪኑ የትግራይ ወጣት "አንተም ሙት፣ እኔም ልሙት" ተብሎ እንደ ደረቅ ቅጠል በጦርነት እሳት ሲማገድ፣ መንደሩ ሲፈርስ እና ሚሊዮኖች ሲራቡ፣ የጦርነቱ ጠባሳ ገና ሳይሽር፣ መሪዎቹ ግን በኒውዮርክ ንጹህ አየር እየተነፈሱ፣ ሙሉ ሱፍ ለብሰው ለካሜራ "ቺዝ" ይላሉ። አቤት የሰማይ እና የምድር ርቀት! አቤት የህዝብ እውነታ እና የልሂቃን ቅንጦት!

የፖለቲካችንን ነገር ይበልጥ አስቂኝ የሚያደርገው የአቶ ጌታቸው የትናንት እና የዛሬ ሚና ነው። ትናንት የፌደራል መንግስቱን በጠላትነት ፈርጀው፣ ህዝብን ወደ ጦርነት ሲያመሩ አልነበረም? ዛሬ ደግሞ የዚያኑ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ሹመት ተቀብለው ዲፕሎማሲ ሲሰሩ ማየት፣ ፖለቲካችን ምን ያህል የልብስ ቅያሪ እንጂ የልብ ቅያሪ እንደሌለው ያሳያል። ዶ/ር ቴድሮስም ቢሆኑ፣ በጄኔቫ ሆነው የኢትዮጵያን መንግስት አጥብቀው ሲተቹ እና ሲያወግዙ አልነበሩም? ዛሬ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀኝ እጅ ከሆኑት አቶ ጌታቸው ጋር ሞቅ ያለ የናፍቆት ሰላምታ ሲለዋወጡ፣ "እስስትም የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ቢያይ ቀለሙን መቀየር ያቆማል" ያሰኛል።

ከዚህ ፎቶግራፍ ተራው ዜጋ የሚማረው አንድ መራራ ሀቅ አለ... የፖለቲካ ልሂቃን ደማቸው አይቃባም፤ ጥቅማቸው ሲነካ ይጣላሉ፣ አቋራጭ ሲያገኙ ደግሞ ይተቃቀፋሉ። እሳቱን የሚያቀጣጥሉት እነሱ፣ ማገዶው ደግሞ በስሜት የሚነዳው ምስኪኑ ህዝብ ነው። ጦርነቱ ሲያልቅ ማገዶው አመድ ይሆናል፤ አቀጣጣዮቹ ግን ኒውዮርክ ሄደው ይተቃቀፋሉ። ስለዚህ የኒውዮርኩ ፈገግታ የትግራይን ብሎም የኢትዮጵያን እናቶች እንባ የሚያብስ አይደለም፤ የልሂቃኑን ምቾት እና ግድየለሽነት በታሪክ መዝገብ ላይ የሚያሰፍር አሳዛኝ የካሜራ ብልጭታ እንጂ።

ከአበጀ በለው

14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.