Logo
FastMereja
ሳዲዮ ማኔ በሃገሩ ሴኔጋል በ20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ግዙፍ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አስጀመረ
#fastmereja I የሴኔጋል የእግር ኳስ ኮከብ ሳዲዮ ማኔ በደቡባዊ ሴኔጋል በሚገኘውና በተወለደበት ባምባሊ መንደር የ20 ሚሊዮን ዶላር ግዙፍ የግብርና ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት መሠረት ድንጋይ አኖረ። እንደ DW Africa እና የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘገባ፣ ማኔ በራሱ ኩባንያ 'SM10 Agro' በኩል የሚመራውን ይህን ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በራሱ የግል ገንዘብ የሚሸፍነው ነው።

በ500 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የማንጎ እርሻዎችን፣ አራት የማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን፣ የግብርና ሥልጠና ማዕከልን እንዲሁም የምርምርና ልማት ክፍሎችን ያካተተ ነው።

ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዓመት እስከ 8,500 ቶን ማንጎ የማቀናበር አቅም ይኖረዋል። ፋብሪካው ማንጎን ወደ ተለያዩ ተጨማሪ እሴት ያላቸው ምርቶች እንደ የማንጎ ጭማቂ፣ ደረቅ ማንጎ እና የማንጎ ቅቤ በመቀየር ለአገር ውስጥና ለውጭ ኤክስፖርት ገበያ ያቀርባል።

ማኔ ቀደም ሲል በትውልድ መንደሩ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መስጊድ፣ የነዳጅ ማደያ እና የዳቦ ቤት በመገንባት የሚታወቅ ሲሆን፤ አዲሱ የግብርና ፕሮጀክት ደግሞ ዘላቂ የሥራ ዕድልና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለህብረተሰቡ ለማስገኘት ያለመ ነው። ተጫዋቹ የባምባሊ አካባቢ የሚመረተው በርካታ ማንጎ ማቀናበሪያ በማጣቱ ምክንያት ይባክን እንደነበር ገልጾ፣ "የምድራችን ፍሬ እዚሁ እንዲቀር እና እሴት እንዲፈጠርበት እፈልጋለሁ" ሲል ስለ ፕሮጀክቱ አስፈላጊነት ተናግሯል።

16 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.