Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በታንዛኒያ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበው 'ንጎሮንጎሮ የዱር እንስሳት ጥበቃ ስፍራ፣ 10 አንበሶች በመርዝ ህይወታቸው አልፎ መገኘታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ። እ.ኤ.አ መስከረም 18 ቀን 2026 (Sept 18) የሞቱት እነዚህ አንበሶች በተከለከለ መርዝ ሕይወታቸው እንዳለፈ እና ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።

ይህ አሳዛኝ ክስተት ተራ የሆነ የአደን ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚከተለው የኃይል ፖሊሲ ያመጣው መዘዝ መሆኑን ክስተቱ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የታንዛኒያ መንግሥት "የአካባቢው ህዝብ ቁጥር ከ8,000 ወደ 100,000 ከፍ በማለቱ የእንስሳቱን መኖሪያ አጠበበ" በሚል ሰበብ፣ ከ2022 ጀምሮ ጥንታዊውን የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ በኃይል የማፈናቀል ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል።

ይህ ማኅበረሰቡን ያላማከለ እና የዜጎችን የመኖር መብት የነጠቀ ፖሊሲ፣ ነዋሪዎቹ ከእንስሳቱ ጋር በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጓቸዋል። ማኅበረሰቡ የመሬት ባለቤትነት መብቱን ሲነጠቅ እና ሲፈናቀል፣ መንግሥት "እጠብቀዋለሁ" የሚለውን የተፈጥሮ ሀብት (በተለይም የዱር እንስሳትን) የአጸፋዊ እርምጃው ሰለባ እያደረገው ይገኛል።

በተመሳሳይ ከሰኔ ወር ጀምሮ አጎራባች በሆነው የኬንያ 'አምቦሴሊ' ሥነ-ምህዳር ውስጥ ቢያንስ 20 ዝሆኖች በተመሳሳይ የጸረ-ተባይ መርዝ መገደላቸው፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኑሮ ዋስትና እና ሰብዓዊ መብት ከግምት ውስጥ ካላስገቡ በቀር፣ እንስሳቱንም ቢሆን ከጥፋት ሊታደጓቸው እንደማይችሉ የሚያሳይ ጥልቅ ማሳያ ነው።

17 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.