Logo
SeledaPost
ሁለት ተበዳዮችን በአንድ ለሊት አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ!

የ39 ዓመት ዕድሜ ያለው ተከሳሽ ሰጣርጌ ግሩም በምስራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ ወይራ ጉሬዛም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን፣ በወቅቱ ለሥራ ከተመደበበት ዲማ ቀበሌ ከሥራ ቦታ በመሰወር እተበዳይ ቤት መሄዱን ፖሊስ ገልጿል።

ተከሳሹ የሕግ አካል እንደሆነ በመግለጽ በቤቱ ውስጥ ሌባ ተደብቋል በማለት በሩን አስከፍቶ ወደ ቤቱ እንደገባ ተመላክቷል።

ተከሳሹ ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ የቤቱን በር በመዝጋትና በጦር መሣሪያ በማስፈራራት በቤቱ የነበሩ ሦስት ሰዎች እንዲተኙ ካስገደደ በኋላ_የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እና_ የተባለች  የ20 ዓመት እድሜ ያላት (የመጀመርያዋ ተደፋሪ አክስትን)  ሁለቱን ግለሠቦች እስከ ንጋቱ 11፡00 ሰዓት ድረስ አስገድዶ መድፈሩን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል።

የእነማይ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ሹሜ ላቀው እንደገለጹት በማግስቱ መርማሪ ፖሊሶች በቦታው በመድረስ አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ ካከናወኑ በኋላ ተጠርጣሪውንና ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በምርመራውም በተጎጂዎቹ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈጸሙ መረጋገጡን ኃላፊው ገልጸዋል።

ተከሳሹ ከዚህ በፊት በግድያ ወንጀል የ16 ዓመት እስራት ተፈርዶበት የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ አምስት ዓመት ከታሰረ በኋላ በ2015 ዓ.ም በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ከማረሚያ ቤት አምልጦ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድንን ተቀላቅሎ ሲዋጋ ቆይቷል ተብሏል።

በኋላም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብሎ በመግባት በወረዳው የሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበር ተመላክቷል።

ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በፍጥነት በማጣራት ለእነማይ ወረዳ አቃቤ ሕግ ከላከ በኋላ በተከሳሹ ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል።

የእነማይ ወረዳ ፍርድ ቤትም መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀረቡለትን ማስረጃዎችና የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሁኔታዎችን መርምሮ ተከሳሹ ሰጣርጌ ግሩም በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

የእነማይ ወረዳ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ የፍርድ ውሳኔው በተመሳሳይ ወንጀል ሊሳተፉ ለሚችሉ ግለሰቦች ትምህርት የሚሰጥና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያሳይ ነው።

Seledadotio
Seledadotio
20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.