Logo
YenetaTube
የሳዑዲው ልዑል አሜሪካ በሁቲዎች ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ጠይቀው ተቀባይነት አለማግኘታቸው ተዘገበ

የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ሐሙስ ዕለት ሁለት ጊዜ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልክ ደውለው በየመን በሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ አሜሪካ የአየር ጥቃት እንድትፈጽም መጠየቃቸው ተዘገበ።
አክሲዮስ የተባለው የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ጥያቄውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውድቅ አድርገውታል፤ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት በሁቲዎች ላይ ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ ዕቅድ እንደሌለው ገልጸዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ሳዑዲ የአየር ጥቃቱን ስለመጠየቋ ለማጣራት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ እና በዋሽንግተን ላለው የሳዑዲ ኤምባሲ ጥያቄ ቢቀርብም ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።
እንደ አክሲዮስ ዘገባ፣ አሜሪካ በየመን ውስጥ በፈጣን ሁኔታ እየተባባሰ ያለውን ግጭት በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለችው ሲሆን፣ ነገር ግን ቀጥተኛ ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ ላለመግባት ለሳዑዲ አረቢያ የምትሰጠውን ድጋፍ እያጠናከረች ነው።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ሐሙስ ዕለት ለአስቸኳይ የቅንጅት ውይይት ወደ ሳዑዲ አረቢያ መጓዛቸውም ተዘግቧል።
ዘገባው ጨምሮም የአሜሪካ ወታደራዊ እና ሲቪል ባለሥልጣናት ባለፉት ሳምንታት ለሳዑዲ አቻዎቻቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጡት መመሪያ፣ የአሜሪካ ኃይሎች ትኩረታቸውን በኢራን እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከብ እንቅስቃሴን በመጠበቅ ላይ እንዲያደርጉ፣ ሌላ የወታደራዊ ግጭት ግንባር ከመክፈት እንዲቆጠቡ የሚል መሆኑን ገልጸዋል።

የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ዒላማ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ መርከቦቿ በቀይ ባሕር ደቡባዊ ክፍል በኩል እንዳያልፉ በቡድኑ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፣ የሁቲዎችን ጥቃት ለመከላከልም ከቱርክ እና ከፓኪስታን ጋር ጥምረት ከመመሥረቷ በተጨማሪ ምዕራባውያን የቀይ ባሕርን ደኅንነት በመጠበቅ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርባለች።
በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው ሁቲዎች በሳዑዲ በሚመራው ጥምረት የሚደገፈውን የየመን መንግሥት በማዳከም የአገሪቱን ሰፊ አካባቢ እየተቆጣጠሩ ነው።
ባለፉት ቀናትም ይዞታቸውን እያሰፉ ወደ ቀይ ባሕር የሚሰስገባውን የባብ ኤል መንደብ መተላለፊያ ወሽመጥን ለመቆጣጠር የሚሰስችሏቸውን የየመን ወደቦች እና የባሕር ዳርቻዎችን በእጃቸው አስግበተዋል።

BBC

24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.