Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዳላስ ከተማ በተካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ታሪካዊ የምርጫ ቅስቀሳ መድረክ ላይ ያልተጠበቀ ቃል በመግባት አሜሪካውያንን አስገርመዋል። ትራምፕ በንግግራቸው፣ በመጪው የህዳር ወር አጋማሽ ምርጫ (Midterm election) ሪፐብሊካኖች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እና ሴኔቱን ካሸነፉ፣ ለእያንዳንዱ አሜሪካዊ አዋቂ ዜጋ 5,000 ዶላር በ«ትራምፕ ዲቪደንድ» ስም እንደሚከፍሉ ቃል ገብተዋል።

ይህ ክፍያ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ስኬት እና ከውጭ ምርቶች ላይ ከሚሰበሰበው የታሪፍ ገቢ የሚሸፈን መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን ክፍያ ባለፈው ዓመት ለወታደሮች ከተሰጠው የ1,776 ዶላር ክፍያ ጋር አመሳስለውታል። ሆኖም ይህ ክፍያ ኮንግረሱ ሊያጸድቀው ይገባል ወይ የሚለው ላይ ግልጽ መረጃ አልሰጡም። ከንግግራቸው በኋላ ዴሞክራቶች እርምጃውን በመጪው ምርጫ የሚጠብቃቸውን ሽንፈት ለማስቀረት የተደረገ "ተስፋ የቆረጠ ሙከራ" ሲሉ አጣጥለውታል።

የትራምፕ የ5 ሺህ ዶላር ክፍያ ቃል ትልቅ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክርክር አስነስቷል። በኢኮኖሚው በኩል፣ ይህን ያህል ገንዘብ ለ245 ሚሊዮን አዋቂ አሜሪካውያን ማደል ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ቀድሞውንም በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የአሜሪካን የዋጋ ግሽበት በእጅጉ ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት በኢኮኖሚስቶች ዘንድ አሳድሯል። በፖለቲካው መስክ ደግሞ፣ ይህ ድርጊት መራጮችን በገንዘብ ለመደለል እንደተደረገ የስልጣን ማቆያ ስልት እና "ድምጽ የመግዛት ሙከራ" (Vote buying) ተደርጎ እየተተቸ ይገኛል። በታሪክ እንደሚታየው፣ በስልጣን ላይ ያለው ፕሬዝዳንት ፓርቲ በአጋማሽ ምርጫ ብዙ መቀመጫዎችን ያጣል፤ ትራምፕም ይህን ታሪካዊ ሽንፈት ለመቀልበስ የፈጠሩት አዲስ ስትራቴጂ ይመስላል።

ትራምፕ የገቡት የ5 ሺህ ዶላር ቃል ፖለቲካዊ ትኩረት ለመሳብ የተወረወረ ትልቅ ካርድ ቢሆንም፣ በተግባር ላይ መዋሉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው! ኮንግረሱ እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል ውሳኔ በቀላሉ የሚያጸድቀው አይሆንም። በመሆኑም ይህ ቃል ከአሜሪካውያን የኑሮ ውድነት ጭንቀት ጋር በመጫወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ ስልት መሆኑን መረዳት ይገባል!

27 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.