Logo
FastMereja
በ9 ቀናት ለ60 ሕፃናት ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተሰጠ

በኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ አስተባባሪነት በአንድ ዓመት ለአንድ ሺ ሕፃናት ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት በያዘው ዕቅድ መሰረት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የመጀመሪያ ዙር 60 ሕፃናትን የማከም ተግባር በስኬት ማጠናቀቁን ይፋ አደረገ።

በጅማ ሆስፒታል ወረፋ ቅደምተከተል መሰረት ለ200 ያህል ሕጻናት የልብ አልትራሳውንድ ምርመራ - (Echo) ተከናውኖ ለ60 የልብ ሕሙማን ነፃ የቀዶ ሕክምና በመስጠት ለልጆቹ እፎይታ ከማስገኘት በተጨማሪ በተለይም የእናቶችን እምባ ማበስ መቻሉ ትልቁ ስኬት ነው ብለዋል።

በ2019 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ በ10 የተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች ለቀሪዎቹ 940 ሕፃናት ነፃ የቀዶ ሕክምና የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ብርሃን ተድላ የኸርት ቱ ኸርት ቺልድረንስ ኤይድ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ተናግረዋል።

የመርሐግብሩ ዋና ዓላማ በአቅምና በትራንስፖርት እጥረት ወደአዲስአበባ ከተማ መጥተው መታከም የማይችሉ የልብ ሕሙማን ባሉበት ለመድረስና ሕክምናውን ከመስጠት በተጨማሪም ከአዲስአበባ ውጪ የሚገኙ የመንንግሥት ሆስፒታሎችና ባለሙያዎች የልብ ሕክምና አገልግሎት ራሳቸውን ችለው እንዲሰጡ የሥልጠናና የእውቀት ሽግግር እንዲያገኙና አገልግሎቱን እንዲቀጥሉ ለማገዝ መኾኑን አቶ ብርሃን ተናግረዋል።

በመርሐግብሩ ላይ ለተሳተፉ የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና የጣልያን ቮቼ ፓድሪ ፒዮ እና CCPM አመራሮችና የሕክምና ባለሙያዎች ለላቀ ተግባራቸው የምስጋና እና የእውቅና መርሐ ግብር በጅማ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት መከናወኑም ተጠቁሟል።

አቶ ብርሃን በመጨረሻም በተያዘው ዕቅድ መሰረት በአንድ ዓመት አንድ ሺህ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ጋር ለመድረስ እንዲቻል በሀገር ውስጥ ኾነ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ የመንግሥትና የግል ተቋማት መርሐግብሩን በገንዘብና በዓይነት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ለነፃ የልብ ሕክምና ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው የጣልያን የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ጳጉሜን 2 ማምሻውን ወደሀገሩ በክብር መሸኘቱም ተገልጿል።

በመጨረሻም አቶ ብርሃን ተድላ በመርሐግብሩ ለተሳተፉ፣ ድጋፍ ላደረጉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣በሥራው የተሳተፉ የሕክምና ቡድን አባላት፣ የዳርክ ብሉ ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሙሉአለምና ባልደረቦቻቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና እና የእድገት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

28 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.