Logo
Getu Temesgen
ከአሰቃቂው ምሽት እስከ ዳግም ተስፋ
የሎሪስ ካሪየስ የትግል ጉዞ

✍️ በጋዜጠኛ ብሩክ ተስፋዬ
#ethiopia | በ2018 በዩክሬን ኪዬቭ የተካሄደው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ለሪያል ማድሪድ የድልና የክብር፣ ለሊቨርፑል ደግሞ የልብ ስብራት ምሽት ነበር። ነገር ግን ከዚያ ምሽት የበለጠ የተጎዳው የ24 ዓመቱ ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ ሎሪስ ካሪየስ ነበር።

በዚያ ታሪካዊ ምሽት ካሪየስ ለሊቨርፑል በጣም ከባድ የሆኑ ሁለት ስህተቶችን ሰርቷል። የመጀመሪያዋ ግብ ከእጁ ላይ በቀረችው ኳስ ከካሪም ቤንዜማ ጋር ተያይዛ ሲሆን፣ በኋላም ጋሬዝ ቤል ከሩቅ የመታትን ኳስ መቆጣጠር ተስኖት ሁለተኛዋ ግብ ሆና ጨዋታው 3-1 በሪያል ማድሪድ እጅ ተጠናቀቀ።

ያ ምሽት ለካሪየስ ግን የአንድ ጨዋታ ሽንፈት ብቻ አልነበረም። በደጋፊዎች ትችት፣ በማህበራዊ ጫናና በስሜታዊ ጉዳት የተሞላ አስቸጋሪ ዘመን መጀመሪያ ሆነ። ብዙዎችም የእግር ኳስ ህይወቱ እዚያው እንደተቋጨ ያህል ተመለከቱት።

ከውድቀት ወደ ዳግም መነሳት

ከሊቨርፑል ከተለየ በኋላ ካሪየስ በተለያዩ ክለቦች አስቸጋሪ ዓመታትን አሳልፏል። ይሁንና ተስፋውን ሳይቆርጥ ለመመለስ ታገለ።

በመጨረሻም ወደ ጀርመኑ ሻልከ 04 መዛወሩ ለካሪየስ አዲስ ምዕራፍ ከፈተለት። በክለቡ ውስጥ ዳግም ራሱን ለማሳየት በጽናት መስራቱን ቀጠለ።

ባለፈው የውድድር ዘመንም በ12 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር በማጠናቀቅ የቀድሞ ብቃቱን ዳግም ማስመስከር ችሏል።

በባየርን ፊት የተገኘ ትልቅ ፈተና

በቅዳሜ ምሽት በቬልቲንስ አሬና በተካሄደው የሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ፣ ሻልከ ከኃያሉ ባየርን ሙኒክ ጋር ተገናኘ።

ካሪየስም የባየርንን አደገኛ የማጥቃት ኃይል በጽናት ተቋቁሞ፣ መረቡን ሳያስደፍር ጨዋታውን 0-0 አጠናቀቀ። ይህም ለሻልከ ውድ አንድ ነጥብ አስገኘ።

የካሪየስ ታሪክ የሚያስተምረው

የሎሪስ ካሪየስ ጉዞ አንድ ነገር በግልጽ ያሳያል፤ አንድ ስህተት የሰውን ሙሉ ህይወት አይወስንም።

አንድ አሰቃቂ ምሽት ሊያሳፍር ይችላል፤ አንድ ውድቀት ሊያሳምም ይችላል፤ ነገር ግን በጽናት እና በጠንካራ ስነ-ልቦና ከቀጠልን ዳግም መነሳት ይቻላል።

ካሪየስ የግብ ጠባቂነት ታሪክ ብቻ አይደለም—ከውድቀት በኋላ ዳግም ስለመነሳት የሚናገር ህያው ታሪክ ነው።
#loriskarius #schalke04 #liverpool #realmadrid #bayernmunich #football #championsleague #የእግርኳስታሪክ #ጽናት #ዳግምመነሳት

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.