Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ መዝናኛ ዜና) ድምጻዊ ሳሚ ዳን ትናንትየተካሄደውን የድብልቅ ማርሻል አርት እና የቦክስ ውድድር አስመልክቶ በቪድዮ ትንታኔ ሰጥቷል። ድምጻዊው በዚሁ የቪዲዮ መልእክቱ ላይ በተለይም ታይሰን፣ ንቃተ ህሊና፣ ሮቤል፣ ሴዶ እና ጆኒ የተባሉትን ተወዳዳሪዎች ብቃት እና የስነ ልቦና ዝግጅት በስፋት ገምግሟል።

በመልእክቱ መጀመሪያ ላይ ታይሰን የተባለውን ወጣት ተወዳዳሪ አቅም ያደነቀው ሳሚ ዳን፣ ነገር ግን በውድድሩ ላይ ያሳየው ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን እና ትምክህተኝነት ትኩረቱን እንደሚሰርቀው ተችቷል። ተወዳዳሪው ተጋጣሚው ላይ ከማሾፍ እና ከመዘናጋት ተቆጥቦ ትኩረቱን በጨዋታው ላይ ብቻ ቢያደርግ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል አሳስቧል።

በሌላ በኩል ንቃተ ህሊና እና ሮቤል ባደረጉት ፍልሚያ ዙሪያ ሰፋ ያለ ትንታኔ የሰጠው ድምጻዊው፣ የንቃተ ህሊናን አስገራሚ መሻሻል እንደ ትልቅ የህይወት ፍልስፍና አቅርቦታል። ንቃተ ህሊና ከዚህ ቀደም ካጋጠመው ከባድ ሽንፈት እና ትችት በመማር የትግል ስልትን በሚገባ ሰልጥኖ ተመልሶ በማሸነፉ፣ ከውድቀት ተነስቶ ክፍተትን በመሙላት ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ማሳየቱን አብራርቷል። ተጋጣሚው ሮቤል በበኩሉ አዳዲስ የትግል ስልቶች እውቀት ባለመኖሩ ምክንያት ለከፍተኛ ሽንፈት መዳረጉን ገልጿል።

በተጨማሪም በሴዶ እና ጆኒ መካከል በነበረው ፍልሚያ ጆኒ ስፖርቱ የጎዳና ላይ ዱርዬነት ሳይሆን የባለሙያዎች መሆኑን በተግባር ማሳየቱን መስክሯል። ሴዶ እስከዛሬ የነበረው ልምድ ከጆኒ ጋር ሲጋጠም ምንም ጥቅም እንዳልሰጠው እና በቀላሉ ተይዞ መሸነፉን አስታውሷል።

ድምጻዊው ለሴዶ ገንቢ ምክር ለግሷል። ሴዶ የውድድር ማስተዋወቅ ስራ ላይ እጅግ ጎበዝ መሆኑን የገለጸው ሳሚ ዳን፣ ይህንን ችሎታውን ከእውነተኛ የትግል አቅም ጋር ማዋሃድ እንዳለበት መክሯል። ማንአለብኝነትን ትቶ ለአንድ ዓመት ያህል አዳዲስ የትግል ስልቶችን ቢማር እና ቢሰለጥን፣ በቀጣይ ዓመት ከፍተኛ አሸናፊ መሆን እንደሚችል ጠቁሟል። የውጭ ሀገር ውድድሮችን ከማሰቡ በፊት በቅድሚያ በሀገሩ ላይ ያለውን ክፍተት ሞልቶ የሀገር ውስጥ አሸናፊ መሆን እንዳለበት በማስታወስ መልእክቱን አጠቃልሏል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.