Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ከሰሞኑ በሜሪላንድ፣ አሜሪካ በድንገተኛ ሁኔታ ህይወታቸው ያለፈው የቲክቶከሯ ሐና እናት፣ ወ/ሮ ደንቤቺ ሶርባጋ ሥርዓተ ቀብር መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ።

ያለፈውን ሳምንት መጨረሻ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የነበረውን የሀዘን እና የሽኝት ጸሎት ሥርዓት ተከትሎ፣ የክቡር እናታችን አስከሬን ወደ ትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ የሚገባ ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም ነገ አርብ ነሐሴ 22 ቀን በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ይፈጸማል።

የሚወዷቸውን የልጅ ልጆቻቸውን ለማስደሰት ለመስቀል በዓል ዝግጅት ቅቤ ሲያነጥሩ አድረው፣ የበዓሉን ድባብ ሳያዩ በድንገት በመኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉ የብዙዎችን ልብ ክፉኛ መስበሩ ይታወሳል። የልጇ የሐና እና የቤተሰቡ ልብ በከባድ ሀዘን ቢደማም፣ ያቺን ጠንካራ የቤተሰብ ምሰሶ በክብር ወደ አገራቸው መልሰው ለመሸኘት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

የሥርዓተ ቀብር እና የሽኝት መርሐ ግብር (አርብ ነሐሴ 22 ቀን)፦
ከጠዋቱ 12:30፦ የክቡር እናታችን አስከሬን ከሀገረ አሜሪካ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ፤ በአባቶች፣ በካህናት፣ በመዘምራንና በቤተሰብ አቀባበል ይደረግለታል።

ከጠዋቱ 3:00፦ ጉዞ ወደ መኖሪያ ቤታቸው።
ከጠዋቱ 4:30 ጀምሮ፦ በመኖሪያ ቤታቸው በጉራጌ ብሔረሰብ የክብር ለቅሶ ሥርዓት (ወርኮ ተባነረ) ይከናወናል።
ከጠዋቱ 5:00 – 6:00፦ በአባቶች ጸሎት ሥርዓተ ፍትሐት በመኖሪያ ቤቱ ይደረጋል።
ከቀኑ 7:30፦ በዝማሬ እየታጀቡ ወደ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ጉዞ ይደረጋል።
ከቀኑ 8:15 ጀምሮ (በተከታታይ)፦ በአውደ ምሕረት አቀባበል፣ በደብሩ ሊቃውንት የፍትሐትና ወረብ፣ የሕይወት ታሪክ ንባብ፣ የአበባ ጉንጉን ማበርከት፣ የቤተሰብ ምስጋና እና የወንጌል አገልግሎት ይከናወናሉ።
ከቀኑ 9:20፦ ሥርዓተ ግብዓተ መሬት በቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ይፈጸማል።
ከቀኑ 9:30 ጀምሮ፦ የነፍስ ይማር እና የመጽናኛ መርሐ ግብር በቤተክርስቲያኑ የሰንበቴ አዳራሽ፣ እንዲሁም በማታ እና በተከታታይ ቀናት በመኖሪያ ቤታቸው ይቀጥላል።

🔴 ጥብቅ ማሳሰቢያ ከቤተሰብ፦

ሥነ-ሥርዓቱን በሚመለከት ቤተሰብ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላልፏል። በመርሐ ግብሩ ወቅት ቀረጻ እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸው ከቤተሰብ ዕውቅና የተሰጣቸው የካሜራና የቪዲዮ ቀረጻ ባለሙያዎች ብቻ ናቸው። በመሆኑም ሁሉም ተሳታፊዎች በስልክም ሆነ በሌላ በማንኛውም መሣሪያ ፎቶ ወይም ቪዲዮ እንዳይቀርጹ ቤተሰቡ በአክብሮት ጠይቋል። ይህንን ሥርዓት በመጠበቅ ለቤተሰቡና ለሥነ-ሥርዓቱ ክብር እንዲሰጥ በትህትና እናሳስባለን።

የፈጣሪ ቃል ለተሰበረው የቤተሰባቸው ልብ መጽናናትን ይስጥ፤ የእናታችንንም ነፍስ በሰላም ያሳርፍ።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.