Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በሰሜን ኢትዮጵያ በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ዳግም የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸውን የድሮ ቪዲዮዎች በማቀነባበር እያሰራጩ መሆኑን ኤኤፍፒ (AFP) ፋክት ቼክ ባወጣው ዘገባ አጋልጧል። እነዚህ የሀሰት ምስሎች መከላከያ ሰራዊቱ መቐለን እንደተቆጣጠረ እና የህወሓትን ኃይል እንዳደቀቀ ለማስመሰል ያለሙ ናቸው።

ዘገባው እንደ አብነት ካቀረባቸው የሀሰት መረጃዎች መካከል; የጦር ድሮን የህወሓትን ተሽከርካሪዎች ሲያወድም ያሳያል የተባለው ቪዲዮ ይገኝበታል። ይህ ምስል በእርግጥ በማርች 2025 በአማራ ክልል የተቃጠሉ የጭነት መኪናዎችን የሚያሳይ የድሮ ቪዲዮ ላይ የድሮን ምስል በማቀነባበር የቀረበ ነው።

በተመሳሳይ መከላከያ ሰራዊቱ መቐለን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እንደ ሰበር ዜና የሚያቀርበው ሌላኛው ቪዲዮ፣ በህዳር 2020 የተላለፈን የኢቢሲ አሮጌ ዜና እና በጁላይ 2026 የደቡብ ዕዝ ያደረገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ምስል በማቀላቀል የተሰራ መሆኑ ተረጋግጧል።

የሰላም እና ግጭት ጥናት ምሁር የሆኑት ኬቲል ትሮንቮል እንደሚያስጠነቅቁት፣ የሀሰት መረጃዎችን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም የጠላትነት ስሜትን በማባባስ፣ ግጭትን ለማርገብ እና ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያደናቀፈ ይገኛል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.