Logo
EBC
አርሰናል ከ ኮቨንትሪ ሲቲ - የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታ
***********************

በመጀመሪያው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4:00 ሰዓት ሻምፒዮኑ አርሰናል አዲስ አዳጊውን ኮቨንትሪ ሲቲን በኢሚሬትስ ያስተናግዳል።

በፕሪሚየር ሊጉ ከ22 ዓመታት በኋላ ሻምፒዮን የሆነው አርሰናል ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት ሁሉንም የመክፈቻ ጨዋታዎቹን በድል ጀምሯል። በተለይም መድፈኞቹ ወደ ሊጉ አዲስ ከሚመጡ ቡድኖች ጋር በሜዳቸው ባደረጓቸው ያለፉት 45 ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዳቸው ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ የሞራል የበላይነት ይሰጣቸዋል።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ዛሬ ምሽት በጨዋታው ቡድናቸውን ለድል ካበቁ ከፔፕ ጋርዲዮላ፣ ከጆዜ ሞሪንሆ፣ከየርገን ክሎፕ እና ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በመቀጠል በታሪክ በ249 ጨዋታዎች 150 የፕሪሚየር ሊግ ድሎችን ያስመዘገቡ አምስተኛው አሰልጣኝ በመሆን ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፍራሉ።

በተቃራኒው እንግዶቹ ኮቨንትሪ ሲቲዎች ከ25 ዓመታት ረጅም የሊጉ ቆይታ በኋላ ወደ ታላቁ መድረክ ተመልሰዋል። ይህ ረጅም ቆይታ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ በአንድ ቡድን የተመዘገበ ከፍተኛው ጊዜ ነው።

በቀድሞ የቼልሲ ኮከብ ፍራንክ ላምፓርድ የሚመሩት ኮቨንትሪዎች፣ ምንም እንኳን በ1993 የውድድር ዘመን መክፈቻ አርሰናልን በሜዳው 3 ለ 0 ያሸነፉበት ትዝታ ቢኖራቸውም፣ ከዚያ በኋላ ባደረጓቸው 14 የሊግ ግንኙነቶች ግን ማሸነፍ የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

አርሰናል ወሳኞቹን ተከላካዮች ዊሊያም ሳሊባን እና ዩሪየን ቲምበርን በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የማያገኝ ሲሆን፣ በኮቬንትሪ በኩል ደግሞ ሀጂ ራይት በተመሳሳይ ምክንያት እንደማይሰለፍ ታውቋል።

ዛሬ በሚደረገው በዚህ የመክፈቻ ጨዋታ፣ አርሰናል አሸንፎ ይወጣ ይሆን? ወይስ ኮቨንትሪ? ግምታችሁን አጋሩን።

በዘረንቶስ ሰለሞን
#arsenal #coventrycity #premierleague #epl #arteta #lampard #football #matchday #ebcdotstream

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.