Logo
EBC
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በተግባር፡ ከነዳጅ ጥገኝነት ወደ ዘላቂ ታዳሽ ኃይል
***********************

በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካዊ መናወጦችና ቀውሶች በተለይም የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ የሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በተደጋጋሚ የሚጋረጡት የፀጥታ ስጋቶች በነዳጅ አስመጪ ሀገራት ላይ የፈጠሩት የጥገኝነት ፈተና እጅግ የከፋ ሆኖ ታይቷል።

ከእነዚህ እና መሰል ተደራራቢ ዓለም አቀፍ ክስተቶች በመነሳት ኢትዮጵያ የጀመረችው የነዳጅ ጥገኝነትን የመስበር እና ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመሸጋገር ስትራቴጂ ምን ያህል አርቆ አሳቢነት የታከለበት መሆኑ በተግባር እየታየ ነው።

የውጭ ምንዛሬን ጠራርጎ የሚወስደውን እና የሀገር ሀብትን የሚያባክነውን የነዳጅ ድጎማ በግለሰቦች ደረጃ በማስቀረት ሀብቱን ለብዙኃን ትራንስፖርት እና ለዘላቂ ልማት የማዋል ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በዚሁ መሠረት ያገለገሉ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ እገዳ በመጣል በአንፃሩ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ የተዘረጋው አሠራር የዚሁ አረንጓዴ ትራንስፖርት ወይም ‘ግሪን ሞቢሊቲ’ ስትራቴጂ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ይህ የታዳሽ ኃይል እና አረንጓዴ ትራንስፖርት ሽግግር በመንግሥት የፖሊሲ ማዕቀፍ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በመሬት ላይ በሚታዩ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ጭምር የታጀበ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ በመከናወን ላይ ያሉት የኮሪደር ልማቶች በተለይም የብስክሌት እና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች ደረጃውን የጠበቀ የስማርት ከተማ ግንባታ ማሳያ ናቸው።

ከጥራት አንፃርም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የግራናይት ንጣፍ እና ዘመናዊ መብራቶች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ አነስተኛ የካርቦን ልቀት ላለው የትራንስፖርት ሥርዓት ምቹ ምህዳር ፈጥረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የሚገቡት በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶቡሶች፣ የነዳጅ ጥገኝነትን በዘላቂነት ከመቅረፍ አኳያ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

ከኃይል እና ትራንስፖርት ሴክተር ባሻገር ኢትዮጵያ ይህን የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ከምግብ ሉዓላዊነት ጋር በማስተሳሰር በመስኖ ልማት እና በግድቦች ግንባታ ያገኘችው ስኬት ሀገራዊ የመቋቋም አቅሟን በእጅጉ አጠንክሮታል።

እነዚህ ሁሉ እርስ በርስ የተሳሰሩ ፕሮጀክቶች፣ ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር ያረጋገጡ እርምጃዎች ናቸው።

ከአረንጓዴ ዐሻራ እስከ አረንጓዴ ሞቢሊቲ የተስተዋለው ይህ ተጨባጭ እርምጃ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተምሳሌት አድርጎ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) እንድታስተናግድ የዲፕሎማሲ ድል ያቀዳጃት ነው።

በበረከት ሽመልስ
#ethiopia #greenenergy #cleanenergy #greenmobility #energysovereignty #cop32 #fuel #ebc

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.