Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ሰላም ለመታረቅ ጥሪ አቀረበች፡፡ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት ሊ ጄ ማዩንግ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለው ጦርነት በይፋ እንዲቋጭ ለፒዮንጊያንግ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የደቡብ ኮሪያ 81ኛ የነፃነት በአል ዛሬ በተከበረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ‹‹አንዳችን ሌላችንን ከማስፈራራት ተቆጥበን ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ጦርነት ለማቆም ውይይት እንጀምር›› በማለት ለሰሜን ኮሪያ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ ሂደት እያደገ የመጣውን የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌይር ለመግታት የሚያስችል ውይይት ለማድረግ እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት የተከፈሉት ኮሪያዊያን ከ1950 እስከ 1953 ያደረጉት ጦርነት የቆመ ቢሆንም እስካሁን የሰላም ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ፕሬዝደንት ሊ በዛሬ ንግግራቸው ‹‹ሁለቱ ኮሪያዎች እርስ በእርስ መከባበር ይገባቸዋል፡፡ አላስፈላጊ ግጭቶችንም ማስቆም ይኖርባቸዋል›› ካሉ በኋላ ይህ የሚጀምረው ጥላቻን በመቀነስና በደንብና በስርአት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሲከናወን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አስከትለውም ‹‹ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ፊት ለፊት ተቀምጠው በሰላም አብሮ ስለመኖርና የጋራ እድገት ይመክራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከሰሜን ኮሪያ ይሁንታ ካገኘሁ የኮሪያን ባህረ ሰላጤ የተረጋጋ አደርጋለሁ›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ይህንን ንግግር ያደረጉት ከአሜሪካ ጋር የሚያደርጉትን አመታዊ የ11 ቀናት ወታደራዊ ልምምድ ለመጀመር 24 ሰአታት ሲቀራቸው ነው፡፡ ይህንን ልምምድ ሰሜን ኮሪያ አጥብቃ እንደምትቃወም መግለጿ ይታወሳል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.