Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ኡጋንዳ ስደተኞች በፈቃደኝነት ወደአገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበች፡፡ የኡጋንዳ የአደጋ ዝግጁነትና ስደተኞች ሚኒስትር ሳም ኢንጎላ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ወደመጡበት አገር መመለስን እንዲያስቡበት ያሳሰቡ ሲሆን ለዚህም የሰጡት ምክንያት የሰብአዊነት ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን ነው፡፡

ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት አገራቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ብትገኝም ለእነዚህ ስደተኞች ከሚያስፈልገው በጀት በ50 ፐርሰንቱ ብቻ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በዚያ ላይ በየአመቱ የሚገቡ አዳዲስ ስደተኞች እየጨመሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ 17,458 የብሩንዲ ዜጎች በፈቃዳቸው ወደአገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን ጨምረውም ‹‹ሌሎች ስደተኞችም የብሩንዲዎችን መንገድ መከተል ትክክለኛ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሚሰጠን ድጋፍ ቆሟል፡፡ ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል ገንዘብ የለንም፡፡ አሁንም እየሰራን ያለነው በኪሳራ ነው፡፡ እርዳታ እያደረግን ያለነው እኛ ነን›› በማለት ገልፀዋል፡፡ አስከትለውም ‹‹ጦርነትን በመሸሽ የሚሰደዱ አዳዲስ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህን በሀይል ውጡ ብለን ወደሞት አንልካቸውም፡፡ ምክንያቱም ኡጋንዳ እንግዳ ተቀባይ በመሆኗ ትቀበላቸዋለች›› ያሉት ሚኒስትሩ አንፃራዊ ሰላም ካለባቸው አገራት የተሰደዱ ግን ወደአገራቸው በፈቃዳቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረባቸውን ሞኒተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.