Logo
SeledaPost
ከሁለት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የወንዶች አልባሳትን የሰረቁ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ/ም ከሌሊቱ 9 ሠዓት በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 1 መቻሬ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ደብሩ መለሰ፣ ሞገስ ተካይ፣ ብርሃኑ አያሌው፣ ዘሪሁን በለጠ፣ ሚሊዮን መስፍን እና አብዱልሰላም ነስረዲን የተባሉ ሲሆኑ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3 B 40762 አዲስ አበባ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ በመጠቀም አንድ የወንዶች አልባሳት መሸጫ ሱቅ ገንጥለው ገብተዋል።

ግምታዊ ዋጋቸው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የወንዶች ሱሪ፣ ጫማ እና ቲሸርቶችን ሰርቀው ሊሰወሩ ሲሉ ድርጊቱን በተመለከቱ ግለሰቦች እና በፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ፖሊስ በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ባደረገው ፍተሻ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ከሰረቁት የጎማ ጎሚኒ እና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ጋር  በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ ገልጾ ተገቢውን ማስረጃ በማጠናቀር ክስ እንደሚያስመሰርትም አስታውቋል፡፡

የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ጨለማን እና ዝናብን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የንግድ ተቋማትም ሆኑ ድርጅቶች የጥበቃ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

Seledadotio
Seledadotio
11 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.