Logo
EBC
ተንቀሳቃሽ ቤተ-መጽሐፍት፡ ስልክ ላይ የማቀርቀርን አዚም የሰበረው ባለታክሲ
********************

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች አብዛኛውን ጊዜ በሙዚቃ ጩኸት፣ በትራፊክ ጫጫታና በጉዞ ድካም አዙሪት ውስጥ በመቆየት ይታወቃሉ።

ተሳፋሪውም ታክሲ ውስጥ እንደገባ አንገቱን ደፍቶ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ መንሸራሸር የዘመናችን የተለመደ እውነታ ሆኗል። ወጣት ሰሎሞን አማረ ግን፣ የራሱን ሜትር ታክሲ ከዚህ አሰልቺ እና የተለመደ ምህዋር በማውጣት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ወደ የሚሽከረከር "ተንቀሳቃሽ ቤተ-መጽሐፍት" ቀይሮታል።

በንግድና በጥድፊያ በሚታወቀው የመርካቶ ሰባተኛ ሰፈር ተወልዶ ያደገው ሰሎሞን፣ ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ከዲጂታል ሚዲያው መስፋፋት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ፣ በተለይም ወጣቱ፣ ከመጽሐፍት እየራቀ መምጣቱ በእጅጉ አሳስቦታል። በዚህም የተነሳ፣ ላለፉት ጥቂት ወራት ታክሲውን የዕውቀት ማዕከል በማድረግ ልዩ ልዩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን ለተሳፋሪዎቹ እንደ አዲስ አማራጭ ማቅረብ ጀምሯል።

ሁሉም ሰው ስልኩ ላይ ባቀረቀረበት በዚህ ዘመን፣ ሰሎሞን የታክሲው ውስጥ መደርደሪያዎች ላይ መጽሐፍትን በማስቀመጥ የሰዎችን ትኩረት ወደ ንባብ ለመመለስ የራሱን የትግል ስልት ነድፏል።

ሰለሞን ወደ ታክሲው ለሚገቡ መንገደኞች የሚያቀርበው ሞቅ ያለ ፈገግታና ሰላምታን ብቻ አይደለም፤ በስርዓት የተደረደሩ የዕውቀት ማህደሮችንም ጭምር እንጂ። የትራፊክ መጨናነቅን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ተሳፋሪዎች በጉዞ ወቅት መጽሐፍትን እንዲያነቡ ይጋብዛል።

የጀመሩት መጽሐፍ ልባቸውን ከሰረቀው ደግሞ፣ እዚያው ታክሲ ውስጥ ገዝተውት መንገዳቸውን ያለመሰልቸት በዕውቀት ታጅበው ያጠናቅቃሉ። ይህ አሰራር ከማህበራዊ ሚዲያ ጩኸት ለተወሰኑ ደቂቃዎችም ቢሆን አእምሮን የሚያሳርፉበት ልዩ የጉዞ ተሞክሮ ሆኗል።

የሰሎሞን አካሄድ የንባብ ባህልን ከማበረታታት ባለፈ፣ የገበያ ጥናትን (Marketing Management) ከተግባር ጋር ያዋሃደ አዲስ የስራ ፈጠራ ነው።

ጊዜን ወደ እሴት መቀየር፡ የታክሲ ተሳፋሪን የትራፊክ ውስጥ የባከነ ጊዜ ወደ ምርታማ የገበያ ሰዓት ቀይሮታል።

ድርብ ገቢ፡ ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ባሻገር፣ መጽሐፍትን በመሸጥ የራሱን የገቢ ምንጭ አሳድጓል።

ማህበራዊ ካፒታል፡ "ተሳፋሪዎች የሚሰጡት አዎንታዊ ምላሽና አስደናቂ ስሜት ለስራዬ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥርልኛል" የሚለው ሰሎሞን፣ በየቀኑ ከሚያገኛቸው አዳዲስ ሰዎች ጋር የሚያደርገው ገንቢ ውይይት ከገንዘብ በላይ የሆነ ትልቅ የህይወት ስንቅ እንደሆነለት ይናገራል።

የሰሎሞን አስገራሚው ጎን የዲጂታል ዓለሙን ሙሉ በሙሉ መሸሹ ሳይሆን፣ ቴክኖሎጂውን ለራሱ ዓላማ ማዋሉ ነው። "Sol Books" በሚል ስያሜ በቲክቶክና በሌሎች ማኅበራዊ ገጾች መጻሕፍትን በማስተዋወቅ፣ ዲጂታል ትውልዱን በዲጂታል መድረክ እየቀሰቀሰ ይገኛል።

የዚህ አብዮተኛ ወጣት መልዕክት አጭር እና ግልጽ ነው፦ የተለመደውን አሰራር በመስበር ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም ይህን መሰል በጎ ተግባር ቢያራምዱ፣ ታክሲዎቻችንን ከትራፊክ ጫና ማምለጫነት አልፈው የዕውቀት፣ የሰላምና የፈጠራ ማዕከል ማድረግ ይቻላል።

በሊያ ተስፋዬ

Ethiopian Broadcasting Corporation FM Addis 97.1 /ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ/ #መጽሀፍ #ንባብ

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.