Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት)) አደጋው ከተፈጸመ እነሆ አንድ ወር አልፎታል። የ50 ዓመቷን ኢትዮጵያዊት ሰርክአዲስ አበበ በቀለን ህይወት በከፍተኛ ስካር አሽከርክራ የቀጠፈችው የ28 ዓመቷ ማሪ ባህንድዋ፣ አሁን ላይ እስከ 20 ዓመታት ሊደርስ የሚችል የጽኑ እሥራት ፍርድ ከፊቷ ተደቅኗል። በጆርጂያ ግዛት ህግ መሰረት፣ አንደኛ ደረጃ የተሽከርካሪ ግድያ ብቻውን ከ3 እስከ 15 ዓመት የሚያስቀጣ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር የተደራረቡት ሁለት የDUI (በስካር ማሽከርከር) እና የቸልተኝነት ወንጀሎች ሲታከሉበት፣ ማሪ የወጣትነት ዘመኗን ሙሉ በጨለማ የብረት አጥር ውስጥ እንድታሳልፍ ሊያደርጋት ይችላል።

ነገሩን ይበልጥ አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ የሚያደርገው ከግድያው ጀርባ ያለው የአደጋው መነሻ ምክንያት ነው። ማሪ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን የነፍስ ደጋፊ ነበረች። አደጋው ከመከሰቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በአትላንታ ከተማ የተካሄደውን የኮንጎ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ስትከታተል እና በከፍተኛ ስሜት ስታከብር ውላለች። በዚያች ሌሊት በከፍተኛ ስካር ውስጥ ሆና ስታሽከረክረው የነበረው ጂፕ (Jeep Wrangler) መኪናዋ ላይም፣ የኮንጎ ደጋፊ መሆኗን የሚገልጹ ጽሁፎች እና መፈክሮች ተለጥፈውበት ነበር።

የኮንጎን እግር ኳስ ጨዋታ ድምቀት በከፍተኛ የአልኮል ስካር ታጅባ ስታከብር ያመሸችው ማሪ፣ የራሷን የደስታ ምሽት በንጹህ እግረኛ ደም አጥቅራዋለች። በዚያች የጭለማ ሌሊት ኮርትላንድ አቬኑ ላይ መንገዱን በሰላም እያቋረጠች የነበረችው ምስኪን ኢትዮጵያዊት፣ በመኪናዋ ላይ የኮንጎን መፈክር በለጠፈች እና ራሷን መቆጣጠር ባቃታት ሰካራም አሽከርካሪ የህይወት ጉዞዋ በድንገት እና በአሰቃቂ ሁኔታ ተቋጭቷል።

የአንዲት ሀላፊነት የጎደላት ግለሰብ የደስታ ስካር፣ የአንድን ኢትዮጵያዊት ቤተሰብ ለዘለዓለማዊ የሀዘን ማቅ አልብሷል። አሁን ፍርድ ቤቱ ማሪን ከህብረተሰቡ በማግለል ተመጣጣኝ የሆነውን የጽኑ እሥራት ቅጣት ያስተላልፋል ተብሎ በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ አሳዛኝ ክስተት ግን በስካር የሚመጣ የሰከንድ ስህተት የሁለትን ሰዎች (የገዳይን እና የሟችን) ህይወት እንዴት ለዘለዓለም በጨለማ እንደሚያጠፋው ቁልጭ አድርጎ ያሳየ መሪር ትምህርት ሆኖ አልፏል።

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.