Logo
FBC
በአረንጓዴ ዐሻራ ወደ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሻገረችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ ያለመው ሀገራዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ፤ ዛሬ በአንድ ጀንበር ከ800 ሚሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል ታሪካዊ መርሃ ግብሩን በስኬት እያከናወነ ይገኛል።

የዘንድሮውን ሀገራዊ የችግኝ ተከላ እና የደረሰበትን ምዕራፍ አስመልክቶ የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አረንጓዴ አሻራ በሀገር ውስጥ ካመጣው ሥነ-ምህዳራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ባሻገር ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት በከፍተኛ ሁኔታ የሙቀት መጨመር፣ የደን ሽፋን መመናመን፣ የዱር እንስሳት ስደት እና የግብርና ምርታማነት መቀነስ የመሳሰሉ ችግሮች እየጨመሩ መጥተው ነበር፡፡ ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀልበስ የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን ዶ/ር አደፍርስ ገልጸዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉም ዜጋ እና ተቋማት በአንድነት በተሳተፉበት በዚህ ንቅናቄ፤ አሳሳቢ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23.6 መድረስ ችሏል።

ኢትዮጵያ ባከናወነችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም በየዓመቱ እስከ 92 ሺህ ሄክታር ይደርስ የነበረው የደን ጭፍጨፋ አሁን ላይ ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ማድረግ ተችሏል።

በመርሃ ግብሩም የደን፣ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖ እና ልዩ ልዩ ችግኞችን በማፍላት እና በመንከባከብ ሂደት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል።

ይህም ለዜጎች የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር አስችሏል።

በአረንጓዴ ዐሻራ የመጣው ድምር ሥነ-ምህዳራዊ ውጤት፤ እንደ ሐረማያ እና አቢጃታ-ሻላ ያሉ የደረቁ እና መጠናቸው በከፍኛ ሁኔታ የቀነሱ ሐይቆች ዳግም እንዲያንሰራሩ ጭምር ትልቅ ሚና መጫወቱን ዶክተር አደፍርስ ወርቁ አብራርተዋል።

እንደ ዶ/ር አደፍርስ ማብራሪያ፣ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ሲጀመር በተለይም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበረ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከእቅዷ በላይ በመትከል እና አጽድቃ በማሳየት ይህንን ትርክት መቀየር ችላለች ብለዋል።

አሁን ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ አየር ንብረት ለውጥ በንድፈ ሀሳብ ከመወያየት ባለፈ፤ የኢትዮጵያን ተግባራዊ ስራዎች እና ውጤቶች በማየት ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ጀምሯል።

ይሄም ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ትሩፋት እንድታገኝ እና ስሟ በበጎ እንዲነሳ ማድረጉ አስተባባሪው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) እንድታዘጋጅ መመረጧ የዚሁ ጥረት ውጤት መሆኑንና፤ ጉባኤውም ትክክለኛው የአፍሪካ ኮፕ እንደሚሆን ዶክተር አደፍርስ አብራርተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ አርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ከሚያጋጥመው የድርቅ ፈተና ከመታደግ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን በመቀልበስ ረገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።

በዓለምሰገድ አሳዬ

20 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.