Logo
Getu Temesgen
አሳዛኝ ታሪክ- የፔቲዲን ሱስ
#ethiopia | ዶክተር ካሳ አደጋ ያጋጥመውና የእጁ አጥንት ይሰበራል። ወደ ድንገተኛ ክፍል ሲሄድ ለህመም ማስታገሻ ፔቲዲን የተባለውን መርፌ ይወጉታል። የስብራቱ ህመም ይጠፋና የደስታ ስሜት ይሰማዋል። ከስብራቱ ቢያገግምም ለህመም ማስታገሻ የወሰደው ፔቲዲን ሱስ ሆኖበት በየቀኑ ብዙ ብልቃጦች ራሱን ይወጋል።

ፔቲዲን የሚፃፈው በልዩ የመድሀኒት ማዘዣ ነው። ዶክተር ካሳ ጓደኞቹ እንዲፅፉለት ይጠይቃቸዋል። መጀመሪያ ላይ ይፅፉለት ነበር። በኋላ ግን የሚወስደው መጠን ከፍ ስላለ "አንፅፍም!" ብለው ከለከሉት። አንዳንድ ባልደረቦቹ ግን እያዘኑለት ይፅፉለታል። የሚወስደው መድሀኒት መጠን ከፍ ሲል ልዩ የመድሀኒት ማዘዣውን ይዞ እራሱ እየፃፈ መግዛት ጀመረ። መድሀኒቱ ውድ ስለሆነ ዶክተር ካሳ አብዛኛው ደሞዙን በመድሀኒት ግዢ ነው የሚያጠፋው። ከባልደረቦቹም በተለያየ ጊዜ ብሮች ተበድሯል።

ዶክተር ካሳ ሱሱን ለማቆም ሞክሮ ያውቃል። ነገር ግን ሳይወስድ ሲቀር ላብበላብ ይሆናል። ተረጋግቶ መስራት አይችልም። ይቅበጠበጣል። መድሀኒቱን ባለመውሰዱ የሚሰማውን ምቾት የሚነሳ ስሜት ለማጥፋት ውሳኔውን ሽሮ ፔቲዲን ይወጋል።

አንድ ቀን ዶክተር ካሳ ሆስፒታሉ የሰጠው ቤት ውስጥ ራሱን ስቶ ተዘርሮ ወድቋል። ክፍሉ ውስጥ የፔቲዲን ብልቃጦች አሉ። መርፌና ሲሪንጅ አጠገቡ አለ....

ዶክተር ካሳ ልቦለዳዊ ስም ይሆን እንጂ ተመሳሳይ የፔቲዲን ሱስ ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ። አብዛኞቹ ደግሞ የጤና ባለሞያዎች ናቸው። ነርሶች፣ የሰመመን ባለሞያዎች፣ ሀኪሞች፣ የፋርማሲ ባለምያዎች...። ህክምና ሞያ ውስጥ ጥቂት አመታት ያሳለፍን ሰዎች በዚህ ሱስ የሚቸገር የምናውቀው ሰው ወይም ወዳጅ አለን።

በሱስ የሚቸገሩ ሰዎች ላይ ፍረጃ ከማድረግ ይልቅ ሞያዊ እገዛ እንዲያገኙ ብናደርግ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ እንችላለን። ሱስ ህክምና ያለው የአእምሮ ህመም ነው።

እኔ የምወደውን ሰው በፔቲዲን ሱስ ምክኒያት አጥቻለሁ። ይመለከተኛል። ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ውስጥ እንዳያልፉና ተገቢውን የአእምሮ ህክምና እንዲያገኙ የምችለውን ያህል ግንዛቤ ለመፍጠር እጥራለሁ።

ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው

14 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.