Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ዛሬ ሰኞ እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ኢራን ይህንን ዛሬ አስተባብላለች፡፡ እነዚህ ሁለት ተቃራኒ አቋሞች በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የሁለቱን አቋሞች በአጭሩ እንግለፅላችሁ፡፡

ፕሬዝደንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር ሰኞ እንደሚቀጥል ገልፀው ድርድሩ በሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይና የኢራንን ኒውክሌይር ጦር መሳሪያ የተመለከተ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በኢራን ላይ ሊያካሂዱት ያቀዱትን ‹‹ከባድ›› ጥቃት ያቆሙትም አጋሮቻቸው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲመርጡ ስላሳሰቧቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ትላንት በሰጡት መግለጫ ‹‹በድርድር መልክ እየተነጋገርን ነው፡፡ ይህም ነገ ከሰአት ይጀምራል፡፡›› በማለት በእርግጠኝነት ተናግረው ነበር፡፡

አጋሮቻቸው ድርድሩ እንደሚደረግና ስምምነት ላይም እንደሚደረስ የነገሯቸው መሆኑን ጠቀሱት ትራምፕ ይህ ካልሆነ ግን ‹‹ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ›› የሚባለውን ጥቃት በኢራን ላይ እንደሚፈፅሙ አስታውቀዋል፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ግን በአሁኑ ጊዜ ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ምንም ድርድር የሌለ መሆኑን ከመግለፃቸውም በላይ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥም ተደራዳሪዎችን የመላክ እቅድ እንደሌላት አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሆርሙዝ ሰርጥን በተመለከተ ድርድር እየተካሄደ ያለው ከኦማን ጋር መሆኑን ጠቅሰው ይህ ድርድር ጥሩ እየሄደ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ይሁንና ከኦማን ጋር በሚደረግ ድርድር ብቻ ሆርሙዝ ሰርጥ እንደማይከፈት አስታውቀው አሜሪካ ጥቃት ከቀጠለች ሁኔታው ባለበት እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በዛሬ መግለጫቸው ከአሜሪካ ጋር ለማደራደር አዲስ አስታራቂ እንዳልመጣ ጠቅሰውም በሽምግልናው እየተሳተፉ ያሉት ፓኪስታንና ኳታር ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ቻይና እየጨመረ በመጣው ውጥረት ስጋት እንዳላት በመግለፅ ተጨማሪ ግጭት እንዳይመጣ እየሰራች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል፡፡ አክለውም የየመንን ሁኔታ ከኢራን ጋር ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረው ‹‹እንዲህ አይነት ጥረቶች ከሀላፊነት ለመሸሽ የሚደረጉ ናቸው›› ብለዋል፡፡

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.