Logo
Getu Temesgen
ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በEVACONET የአርክቴክቸር ዲዛይን ውድድር አንደኛ ሆነ
#ethiopia | አዲስ አበባ – በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የEVACONET ዲጂታል የኮንስትራክሽን ገበያ ፕላትፎርም የምረቃ ሥነ ሥርዓት አካል በሆነው የአርክቴክቸር ዲዛይን ውድድር ባህርዳር ዩኒቨርስቲ አንደኛ ደረጃን በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል።

ውድድሩ በዩኒቨርስቲዎች የአርክቴክቸር ዲፓርትመንት 5ኛ ዓመት ተማሪዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን፣ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ፣ አዲስ ኮሌጅ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። አዘጋጆቹ ውድድሩ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ያስተዋወቀ እንደነበር ገልጸው፣ ከዚህ በኋላም በየዓመቱ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

EVACONET በኢንጂነር አቤሴሎም መለሰ የተቋቋመ ዲጂታል የኮንስትራክሽን ገበያ ፕላትፎርም ሲሆን፣ የኮንስትራክሽን ማቴሪያል ወቅታዊ ዋጋዎችን በማነጻጸር ሻጮችና ገዢዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ የዲጂታል ገበያ ሥርዓት ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር የትምጌታ አስራት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። ተናጋሪዎቹም ፕላትፎርሙ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይን ለማሳካት እንደሚያግዝ፣ በኮንስትራክሽን ገበያ ውስጥ ግልጽነትና ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

በእለቱ "ሕይወትን በኮንስትራክሽን እንገንባ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የኮንስትራክሽን ፋሽን ሾውና የሞዴሎች ትዕይንትም ቀርቦ የተሳታፊዎችን ቀልብ ስቧል።

ዝግጅቱ ለተሳካ አፈጻጸም አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና እና የልዩ ሽልማት ስጦታዎች በመበርከት ተጠናቋል።

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.