Logo
FBC
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽና ቀጣናዊ ፋይዳው

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት አስርት ዓመታት በሰላም ማስከበር፣ በግጭት አፈታት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ ንግድ፣ በቀጣናዊ ትስስር እና በንግድ ትብብር ረገድ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ለጎረቤቶቿ ብሎም ለቀጣናው የምትሰጠውን ከፍ ያለ ትኩረት ያሳያል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የትኛውንም ጎረቤት ሀገር ወርራ አታውቅም፡፡ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ሰላማዊና በትብብር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ጎረቤቶቿ ሰላም በራቃቸው ጊዜ ሁሉ፣ ሰላም ለማስከበር ቀድማ በመገኘት ትታወቃለች፡፡ ይህንንም በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ እንዲሁም ከጎረቤቶቿ ራቅ ብላም በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በኮንጎ እና በሴራሊዮን በተግባር አስመስክራለች፡፡

በአህጉር ደረጃ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩ አፍሪካውያን ወንድም እህቶች ነጻ ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በስልጠና፣ በሎጂስቲክስና በዲፕሎማሲ መስክ ጭምር መደገፏ አሌ የማይባል ሃቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬም የልማት ትሩፋቷን ለብቻዋ ዕድገትና ለውጥ የምትጠቀም ሀገር አይደለችም፡፡ ይልቁንም ልማቷን እና ለውጧን በማጋራት እና ለጎረቤቶቿ አብሮ መለወጥ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በአፍሪካ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አምራች ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ ለጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ኤሌክትሪክ እየላከች ነው።

ይህ በአካባቢው የኢንዱስትሪ ልማት፣ የከተማ እድገት እና የህዝብ ኑሮ መሻሻል ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው።

በንግድ ረገድም ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እና የአፍሪካ ህብረት "አጀንዳ 2063" የሚያስቀምጧቸውን የክልላዊ ውህደት ግቦች ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ የድንበር ንግድ ማዕከላት እና የትራንስፖርት ኮሪደሮችን በማስፋፋት በቀጣናዊ ትስስር ማደግና መጠናከር ላይ ግዙፍ ኢንቨስትመንት እያካሄደች ነው።

ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ሰላምና ደህንነት፣ እድገትና ልማት አበክራ የሰራቻቸው ስራዎች ለቀጣናውና ለሀገራቱ ያላትን አዎንታዊ ሚና በግልፅ ያሳያል። ሀገሪቱ የባህር በር ጥያቄዋ ምላሽ ሲያገኝ ይህ ቀጣናዊ ገንቢ ሚናዋ በምን ያህል መጠን ሊያድግና ሊባዛ እንደሚችል ለመገመት አያዳግትም፡፡

በታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ህዝብ ህጋዊ ስልጣን በሌለው አካል ህጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷን እንድታጣ ተደርጓል፡፡ የመደመር መንግሥት የተፈጸመውን ኢፍትሃዊና ታሪካዊ በደል በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማስመለስ ጥያቄ አቅርቦ የበርካታ ሃያላን ሀገራትን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ካለው ኢኮኖሚዋና የህዝብ ቁጥሯ አንጻር የባሕር በር አማራጭ ሊኖራት ይገባል።

በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የባሕር በር እያለ ኢትዮጵያ ተዘግታ ትኑር የሚል ኢፍትሐዊነት ተቀባይነት የለውም።

የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የንግድ መውጫ መግቢያ ብቻ ሳይሆን፤ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የጂኦፖለቲካ ስትራቴጂ ቁልፍ ጥያቄ በመሆኑ ጥያቄዋ መልስ እስኪያገኝ አበክራ ትሰራለች፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ጥቅሙ ለእርሷ ብቻ አይደለም። በአፍሪካ ቀንድ እና በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመፍጠር ሚና ይኖረዋል፡፡

በአካባቢው የንግድ ኮሪደሮች ስለሚፈጠሩ የወደብ አገልግሎት እንዲስፋፋ፣ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንዲገነቡ በማድረግ የንግድ ትስስርና አዳዲስ የስራ ዕድሎች ለመፍጠር ያስችላል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የምታመነጨው ኤሌክትሪክ ለቀጣናው በበቂ ሁኔታ ማቅረቧ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ይረዳል።

ከዚህ ባሻገር የቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያደገ ሲመጣ በሀገራት መካከል ከግጭት ይልቅ ትብብር እንዲጨምር ያደርጋል። ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በመሠረተ ልማት በተጠናከረ ሁኔታ ሲተሳሰሩ ሰላምን የመጠበቅ ፍላጎታቸውም በዛው ልክ ይጨምራል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት የአፍሪካ ህብረት "አጀንዳ 2063" የሚጠይቀውን ቀጣናዊ ትስስር ለማጠናከር፣ የነፃ ንግድ ቀጣና ለመመስረት እና የመሠረተ ልማት ትስስርን ለማሳካት ጠንካራ መሠረት ለመጣል ያግዛል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ ለማድረግ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ተቋማት ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

9 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.