Logo
Getu Temesgen
በህይወት እያሉ ተመሰገኑ

(በዕዝራ እጅጉ)

.የመዲናዋ ጤና ቢሮ ነፃ ህክምና እንዲያገኙ ወሰነ
#ethiopia | አንጋፋ የሚድያ ባለሙያዎች አዲስ አለም ሓድጉና በልሁ ተረፈ ዛሬ ጋቢ በተደረበላቸው ዕለት ደስታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር።

በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ የማይረሳ አሻራ ያኖሩት እነዚህ ጉምቱ ባለሙያዎች ከ 35 አመት በላይ በትጋት ያገለገሉ ሲሆን በሙያ አጋሮቻቸው ተከበው አድናቆት ሲቸራቸው ውለዋል።

ቅዳሜ ሐምሌ 18 2018 ዓ.ም ከ 4 ሰዓት ጀምሮ በወመዘክር መርስኤሀዘን አዳራሽ በተደረገው መርሀ ግብር የሚድያ ባለሙያዎች እና ወዳጆቻቸው ተገኝተው እኛም አመስጋኞቻችሁ ነን በማለት ለመርሀ ግብሩ ድምቀት ሰጥተዋል።

ባለሙያዎቹን ለማመስገን ራሱን የቻለ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን ይህም ኮሚቴ ባለሙያዎቹ በዘለቄታዊነት የሚታገዙበት መንገድ ያመቻቸ ነው።

ለዝግጅቱ መሳካት በተከፈተው የwhat is up ገፅ ኮሚቴው ውስጥ ተግባራቸውን የተወጡት ጥላሁን ካሣ ፣ሀብታሙ ድረስ ፣ሰለሞን ሀይለኢየሱስ፣ዕዝራ እጅጉ (ተወዳጅ ሚድያ)፣ አለም ታደሰ፣ሠናይት ሀይሌ፣እሸቱ ገለቱ፣ ጌጡ ተመስገን እና ግደይ ገብረ ሲሆኑ እነርሱም በዕለቱ እንደተናገሩት ሥራው በአጭር ጊዜ ታስቦ ለስኬት መብቃቱ ደስ ያሰኛቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለአንጋፋ ባለሙያዎቹ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ነፃ ህክምና የሚያገኙበት መንገድ ያመቻቸ ሲሆን ይህ የመረዳዳት ባህል ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተነግሯል።

አዲስ አለም ሓድጉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትግርኛ ክፍል በኤዲተርነት እና በጋዜጠኝነት የሠራ ሲሆን ላለፉት 35 አመታትም ሙያውን ወዶና አክብሮ በመሥራት ይታወቃል።

የሚድያ ሰው በልሁ ተረፈ ደግሞ በኢትዮጵያ ሬድዮ ከሳይንስ ማህደር፣ ማንነት ሲፈተሽ እና ዝክረ ሰንበት በተባሉ ፕሮግራሞች ከ30 አመት በላይ የሠራ ሲሆን ሌሎችንም በማብቃት የማይዘነጋ አሻራ ለማኖር የቻለ ነው።

"ሰውን በሕይወት ሳለ እናመስግን "የሚል መርህ ያነገበው ይህ መሰናዶ የሚድያ ባለሙያዎችን በኑሯቸው የማገዝ ፣ በችግራቸው ጊዜ አብሯቸው የመሆን ግብ የሰነቀ ነው። እንዲህ አይነቱ ተግባር ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

ሁለቱም ባለሙያዎች አገር የጣለችባቸውን አደራ የተወጡ ብርቱ ባለሙያዎች እንደነበሩ በዕለቱ ምስክርነት የሰጡ ባልደረቦቻቸው የተናገሩ ሲሆን የምስጋና ቀን መዘጋጀቱ አዲስ የሚመጣውንም ባለሙያ የሚያበረታታ ነው ሲሉ ሀሣብ ሰንዝረዋል።

በዕለቱ የሚድያ ሥራን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ያስቃኘ አጭር የትዝታ ዘጋቢ ፊልም የቀረበ ሲሆን ተመስጋኞቹ ከዚህ ቀደም አየር ላይ ያዋሏቸው ሥራዎችም በዕለቱ ለታደሙት እንግዶች ቀርበዋል።

በባልደረቦቻቸው የምስጋና ዝግጅት የተደረገላቸው አዲስአለም ሓድጉና በልሁ ተረፈ እንደዛሬ ደስ ብሎንም አያውቅ ፣ ይህን መርሀ ግብር በተሳካ መንገድ ዕውን እንዲሆን የጣራችሁ ሁሉ ፈጣሪ መንገዳችሁን ያቃና ሲሉ መርቀዋል።

የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል እሸቱ ገለቱ እንዳለው በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የሚሠሩ ባልደረቦች የመጠያየቅ ባህልን ከጀመሩ ሁለት አመት እንደሆናቸው ጠቅሰው ይህ የምስጋና መርሀ ግብር የዚያ መጠያየቅ አካል እንደሆነ ጠቁሟል።

ባለሙያዎች ጡረታ ሲወጡ የሚደገፉበት፣ በተለይም በኢኮኖሚ እገዛ የሚያገኙበት ስልት መነደፍ እንዳለበትም ጋዜጠኛ እሸቱ ጥቆማ ሰጥቷል። በተጨማሪም የጤና ሁኔታቸውን፣ የሚከታተሉበት መንገድ መፈጠር እንዳለበትም ተናግሯል።

ከጡረታ በኃላ ምክር በመስጠት ባለሙያዎቹ ልምዳቸውን ማጋራት አለባቸውም ብሏል።ይህንኑ ትልቅ ርዕይ ለማሳካት መንግሥትና የሚመለከታቸው የሚድያ ማህበራት ሊተባበሩ ይገባልም ሲል ሀሣብ አንስቷል።

የእለቱን የምስጋና መሰናዶ እንዲሳካ አቶ ሠርፀፍሬ ስብሓት አዳራሽ በመስጠት ፣ ጋዜጠኛ ማህደረ ታሪኩ ፕሮጀክተር በመለገስ እንዲሁም አልፋ ውሃ፣ ለታዳሚዎች የመስተንግዶ ውሃ በማቅረብ መርሀ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን አድርገዋል።

11 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.