Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማና አካባቢዋ ያለው የነዳጅ እጥረትና ሕገ-ወጥ ንግድ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱና በአደባባይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገበት መሆኑ ተገለጸ። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አንድ ሊትር ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ ከ600 እስከ 700 ብር እየተቸበቸበ እንደሚገኝና ይህም በሕዝቡና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ከባድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደሩ ተጠቁሟል።

በተለይም በክልሉ በወርቅና በሌሎች የማዕድን አምራችነት ዘርፎች የተሰማሩ ወገኖች በነዳጅ እጥረትና በዋጋው ንረት ሳቢያ ሥራቸውን ለማስቀጠል መቸገራቸውን ገልጸዋል። አምራቾቹ ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን ፈስሰው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢቆዩም፣ አሁን ባለው የነዳጅ ኮንትሮባንድና ዋጋ ንረት ምክንያት ከስረው ከሥራ ውጭ ለመሆን መገደዳቸውን ለዘ-ሐበሻ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪዎችና የማዕድን አምራቾች እንደሚያስረዱት፣ በከተማዋ በሚገኙ ዋና ዋና ማደያዎች (በተለይም ጎመጁ እና የተባበሩት ማደያዎች) ፊትለፊትና በየተለያዩ ቦታዎች ነዳጅ በግልጽ በኮንትሮባንድ መልክ ሲሸጥ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የሚገባቸው አካላት ተገቢውን ቁጥጥርና እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበዋል ሲሉ ይከሳሉ። ድርጊቱ በጸጥታ አካላትና በንግድ ቢሮ በኩል ተገቢውን ክትትል ያጣና በጥቂት ጥቅም ፈላጊዎች የተደራጀ ብልሹ አሠራር ሰለባ የሆነ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አቤቱታ አቅራቢዎቹ የክልሉ መንግሥት እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት በአሶሳ ከተማና አካባቢዋ ያለውን የነዳጅ ስርጭት ግልጽነትና ሕጋዊነት እንዲያረጋግጡ፣ በሕገ-ወጥ ነዳጅ ንግድና ሙስና ላይ የተሰማሩ አካላትን በሕግ እንዲጠይቁ እና ለአካባቢው ማዕድን አምራቾችና ነዋሪዎች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

12 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.