Logo
FBC
ከምርታማነት እስከ ሥራ ፈጠራ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ጸጋን ታድላለች፡፡ ለግብርና የሚስማማ ዓየር ንብረት፣ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች፣ ሊታረስ የሚችል ሰፊ ለም መሬት እንዲሁም ለእንስሳት እርባታ የሚስማማ አየር ሁኔታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተለይም ለምግብነት የሚውሉ የእንስሳትና የእጽዋት ሀብቶቿ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ አድርጓታል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማክሮ ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ቀርጻ ስትተገብር ቆይታለች፡፡

በመደመር መንግሥት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው እንደ አረንጓዴ አሻራ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የሌማት ትሩፋት፣ ገበታ ለሀገር፣ የ5 ሚሊየን ኮደርስ እና የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የሌማት ትሩፋቱ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የስራ እድል ፈጠራን ያበረታታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከወጪ ንግድ የሚገኝ ገቢን የሚያሳድግ እና ከውጭ የምናስገባቸውን የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ይተካል።

ለእንስሳት ተዋጽኦ ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ደግሞ በዘመናዊ መንገድ የተደራጁ የወተት ላሞች ማዕከላትን በመፍጠር የነፍስ ወከፍ የወተት አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል።

በተለያዩ አካባቢዎችም ወተት አምራች አርሶ አደሮች በማህበር በመደራጀት እና ምርታቸውን የሚሸጡበት የገበያ ትስስርን በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል። ይህም ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የወተት ምርት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ያስቻለ ውጤት አምጥቷል።

በመሆኑም መርሐ ግብሩ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተመጣጠነ የምግብ ስርዓት እንዲኖር እያደረገ ነው፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂዋን ለማገዝ የያዘችው ትክክለኛ እና ስኬታማ መንገድ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች በራስ አቅም መለወጥ እንደሚቻል ያሳዩ እና የዜጎችን አምራችነት ያረጋጋጡ ናቸው፡፡

እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ያስቀመጠችውን ግብ ለማፋጠን ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ፡፡ በምግብም ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡

በትዕግስት ግዛቸው

14 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.