Logo
SeledaPost
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ ቪዛ ሰጥታለች- የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

አገልግሎቱ በ2018 የበጀት ዓመት ከ1.04 ሚሊየን በላይ የቪዛ አገልግሎቶችን መስጠቱን ገለፀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ ከሶስት ዓመት በፊት 2መቶ76 ሺህ ቪዛ ብቻ በአመት ውስጥ መስጠቱን አስታውሰው፤ በ2018 በጀት ዓመት 1.04 ሚሊየን ቪዛ በመስጠት ከአራት እጥፍ በላይ እድገት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

አገልግሎቱ የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓቱን ማሻሻሉ፣ የዲጂታል አገልግሎትን ማስፋፋቱና የአየርና የየብስ ድንበር አስተዳደር አገልግሎትን ማዘመኑን ተከትሎ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን በማንሳት አዲስ የተጀመሩት የStopover እና Transit ቪዛ አገልግሎቶች የቱሪዝምና የጉዞ እንቅስቃሴን እያበረታቱ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አክለውም፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1መቶ94 በላይ ሀገራት ዜጎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ  በኢ-ቪዛ (e-Visa)፣ በውጭ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ተቋማት እና በመድረሻ ቪዛ (Visa on Arrival) አማራጮች አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች በማለት የአገልግሎቱን አድማስ አብራርተዋል።

የቱሪዝም ፍሰትን ለማሳደግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትንና የንግድ ግንኙነትን ለማበረታታት እንዲሁም የሰዎችን ነፃ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ የተወሰደ እርምጃ የሀገሪቱን ብልፅግና የሚያፋጥን የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት ያከበረ መሆኑን ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ተናግረዋል።

ወደፊትም ዘመናዊና ቀልጣፋ የቪዛና ሌሎችም የኢሚግሬሽን አገልግሎቶችን በማስፋት እና በማዘመን ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ ተጓዦችና ባለሀብቶች ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

Seledadotio
Seledadotio
15 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.