Logo
FBC
በቅጠሉ ንጹህ አየርን የሚፅፍ፣ በሥሩ አፈርን የሚያፀና

ታሪክ ሁልጊዜ በብዕር ብቻ አይጻፍም፤ አንዳንዴ በእጅ የተቆፈረ ትንሽ ጉድጓድ፣ በውስጡ በተተከለ አንዲት ችግኝ እና በላዩ በተጨመረ አፈር ይጻፋል።

ዛፍ የሚተክል ሰው ለዛሬ ብቻ አይሠራም፤ ያላየውን ትውልድ እያሰበ ይተጋል። ከራሱ ዕድሜ የሚረዝም ተስፋን በምድር ውስጥ ያኖራል። ስለዚህ አንድ ችግኝ መትከል አንድ የወደፊት ምዕራፍ መጀመር ነው።

በዚህ ምክንያት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ዘመቻ ብቻ አይደለም። አንድ ሕዝብ ከተፈጥሮው ጋር የሚያድሰው የታሪክ ውል ነው።

በዚህ ውል ላይ ፈራሚው መንግሥት ብቻ አይደለም። አርሶአደሩ፣ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ሠራተኛው፣ ወጣቱ፣ እናት፣ አባት እና ሕፃን ጭምር ናቸው።

ምክንያቱም አካባቢን መጠበቅ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ አደራ ስለሆነ።

በዚህ ዓመት በ"ተስፋ እንትከል" መሪ ሐሳብ የወደፊት ታሪካችንን በራሳችን እጅ የምንቀርጽበት ነው። ምድር የምትለምልመው በዝናብ ብቻ አይደለም። በሰው ኃላፊነት፣ በሰው ራዕይ እና በሰው ፍቅርም ጭምር እንጂ።

ዛፍ ደግሞ ዝም ብሎ የሚቆም ፍጥረት ሳይሆን በዝምታው ብዙ ነገር ይናገራል። በቅጠሉ ንጹህ አየርን ይጽፋል፤ በሥሩ አፈርን ያጸናል፤ በጥላው ሕይወትን ያቅፋል፤ በፍሬው ተስፋን ያበቅላል። ስለዚህ አንድ ዛፍ መትከል የነገን ሕይወት መትከል ነው።

ዛሬ የዓለማችን ፈተና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን መመናመን፣ የመሬት መራቆትና የውኃ እጥረት ሆኗል። እነዚህን ችግሮች በንግግር ብቻ መፍታት አይቻልም፤ በተግባር የተደገፈ ኃላፊነት ይፈልጋሉ። የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴም የዚህ ኃላፊነት ሕያው መግለጫ ነው።

የዘንድሮው "ተስፋ እንትከል" መሪ ቃል በውስጡ ጥልቅ ፍልስፍና ይዟል።

ተስፋ አይዘራም፤ ይተከላል እንጂ። ምክንያቱም ሥር ማበጀት አለበት፣ በትዕግሥት ማደግ አለበት፣ ፍሬ ማፍራት አለበት። ልክ እንደ ዛፍ።

በዛፍ የሚጀምር ልማት በሀገር ዘላቂ እድገት ላይ ያለውን እምነት በተግባር ያሳያል።

የዘንድሮው ጉዞ በቁጥርም ሲገለጽ ትልቅ ራዕይን ያሳያል። በ2018 ዓ.ም 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

በዚህም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቀደም ሲል የነበረውን 48 ቢሊየን ችግኞች የመትከል ግብ ወደ 56 ቢሊየን ከፍ አድርጎታል። እነዚህ ቁጥሮች የተቆጠሩ ችግኞችን ብቻ አይወክሉም። የሕዝብ ተሳትፎን፣ የሀገር ቁርጠኝነትን እና ለቀጣይ ትውልድ የሚገነባውን አረንጓዴ ተስፋ ይወክላሉ።

ዘንድሮ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ የተከላ መርሃ ግብርም የዚህ ጉዞ ከፍተኛ ምዕራፍ ይሆናል። በመላ ኢትዮጵያ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአንድ ዓላማ ይሰባሰባሉ።

የመደመር መንግሥት አመራሮች፣ የልማት አጋሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተማሪዎች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ ይሳተፋሉ።

ይህ ለሀገር አንድ የጋራ ዓላማ ሲኖር ልዩነቶች ከአንድነት ፊት እንደሚያንሱ የሚያሳይ ተጨባጭ ምሳሌ ነው። ምክንያቱም የዛሬው ችግኝ የነገው ደን ነው፤ የዛሬው አሻራ ደግሞ የኢትዮጵያ የወደፊት ታሪክ ነው።

21 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.