Logo
Getu Temesgen
ቀጣሪና ተቀጣሪን ያገናኘ የአንድ ቀን የሥራ አውደ ርዕይ ተካሄደ

‎#ethiopia | ​በቅርቡ የመቶኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ያከበረውና የ ISO 21001 ዓለም አቀፍ የጥራት ሰርትፍኬት ባለቤት የሆነው ታሪካዊው ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፤ በ2018 ዓ.ም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን በቀጥታ ከሥራ ገበያው ጋር የሚያስተሳስር የሥራ አውደ ርዕይ ተካሄደ

‎በኮሌጁ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውና ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ መድረክ፣ በዋናነት ቀጣሪና ተቀጣሪን በአንድ ጣሪያ ስር በማገናኘት ሰልጣኞች ሥራ ፍለጋ የሚንከራተቱበትን እንዲሁም አሠሪዎች ለቅጥር ማስታወቂያ የሚያወጡትን ጊዜና ወጪ ለመቀነስ ያለመ ነው።

‎የ​ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ መርሃ ግብሩን ለተቋሙና ለሰልጣኞች "ወሰኝ መርሐግብር " ሲሉ ገልጸውታል። ዲኑ እንዳብራሩት፣ ኮሌጁ ስልጠና የመስጠት ብቻ ሳይሆን ተማሪዎቹን ከኢንዱስትሪ ጋር የማስተሳሰር ኃላፊነት ስላለበት ይህንን ተነሳሽነት ወስዷል።

‎አውደ ርዕዩ የራሱን 967 ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ለሚገኙ 14 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተመራቂዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ ጥሪውን ሰምተው ለመጡ የሥራ ፈላጊዎች ሁሉ ክፍት የተደረገ ነበር። ከዚህ ባሻገር፣ ተመራቂዎቹ ለሥራው ዓለም ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ከ "ሟስ ኮንሰልት" ጋር በመተባበር አስቀድሞ የሲቪ አጻጻፍ፣ የቃለ መጠይቅ አቀራረብ ክህሎቶች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

‎​በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት የውጤት ተኮር ልማት ዘርፍ በቢሮ ደረጃ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ በበኩላቸው፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልን ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር ማገናኘት የመንግሥት ዋነኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ መሆኑን ጠቅሰው መድረኩ ያለውን የጎላ ፋይዳ አድንቀዋል።

‎ለዚህ ሁነት መሳካት የ "EASE" ፕሮጀክት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

‎​በአውደ ርዕዩ ላይ ከ30 በላይ ታዋቂ ሆቴሎች፣ የቅጥር መተግበሪያዎች፣ የጋርመንት ኢንዱስትሪዎች፣ የቁጠባና ብድር ማኅበራትና የመገልገያ ዕቃዎች አምራቾች የተሳተፉ ሲሆን፣ በተለይም በኮሌጁ የሥራ ማበልጸጊያ ማዕከል የታቀፉና የ Generative AI ቴክኖሎጂን በመጠቀም ድር ጣቢያዎችን የሚያለሙ የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ሥራ ትልቅ ትኩረትን ስቧል።

‎ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ይህንን ውጤታማ የሥራ ትስስር መድረክ በየዓመቱ ይበልጥ በማሻሻል እንደ ዓመታዊ ቋሚ መርሃ ግብር ለማስቀጠል ማቀዱን አስታውቋል።

‎በጌትነት ተመስገን

‎Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)

‎#getutemesgen #getu #ጌጡ

‎#jobfair #teferimekonnen #addisababa #ethiopiajobs #tvet #careeropportunity #employment #easeproject

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.