Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) አሜሪካ በኢራን የኃይልና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ወታደራዊ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ፣ የየመኑ የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፈውን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመዝጋት ተዋግተው እንዲጠብቁ ቴህራን ጥያቄ ማቅረቧን ሮይተርስ የዜና ወኪል ሦስት የውስጥ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘገበ። ይህ እርምጃ ቀደም ሲል ከተቀሰቀሰው ቀውስ ጋር ተዳምሮ በዓለም አቀፍ የነዳጅና የኃይል አቅርቦት ደኅንነት ላይ አዲስና እጅግ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።

ይህ የውሳኔ ሐሳብ በኢስላማዊቷ ሪፐብሊክ (ኢራን) ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ በስፋት ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ መልእክቱም ለሁቲ ታጣቂዎች መተላለፉን ሁለት ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናትና ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የቀጠናው ምንጮች በምስጢር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስልታዊ ጥያቄ ለሁቲዎች እንዴት እንደተላለፈና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በኢራን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ካስጠነቀቁ በኋላ ስለመሆኑ በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም።

ለሁቲ ቡድን ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ በቀይ ባሕር መግቢያ በሆነው በባቢል መንደብ ስትሬት አቅራቢያ፣ በሁደይዳ ከፍተኛ ቦታዎችና በዓደን ባሕረ ሰላጤ በሚያዋስኑ የመን ከፍተኛ ቦታዎች ላይ በርካታ ሚሳኤሎችንና ድሮኖችን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) በማሰማራት በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅታቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቀው ትዕዛዝ በመጠበቅ ላይ ናቸው። በየመን የሚገኙት የኢራን አብዮታዊ ጠባቂ ጦር (IRGC) ተወካዮች የባቢል መንደብ ስትሬት የሚዘጋበትን ትክክለኛ ጊዜ የመወሰን ሙሉ ሥልጣን እንደሚኖራቸውም ምንጩ አክሏል።

በአሁኑ ወቅት የሆርሙዝ ስትሬት በኢራን ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ባለበት ሁኔታ፣ ሁቲዎች በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች ወይም ወደቦች ላይ አዲስ ጥቃት የሚሰነዝሩ ከሆነ፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሁለቱ ዋና ዋና የነዳጅ ኤክስፖርት መስመሮች በአንድ ጊዜ እንዲስተጓጎሉ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፉ የኃይል ቀውስ ላይ እንዲሁም በኢራንና በአሜሪካ መካከል ባለው ሰፊ ግጭት ላይ አዲስና አስፈሪ ግንባር የሚከፍት ይሆናል።
የቀጠናው የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ቀይ ባሕርን መዝጋት ለሁቲዎች ከባድ አይሆንም። የተራቀቁ ሚሳኤሎች ባይኖሩ እንኳ ማንኛውም መሣሪያ የያዘ አካል በቀላሉ በባሕር ትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ መስተጓጎል መፍጠር ይችላል።

ሳዑዲ ዓረቢያ የሆርሙዝ ስትሬት መዘጋቱን ተከትሎ፣ የነዳጅ አቅርቦቷ እንዳይቋረጥ 70 በመቶ የሚሆነውን የነዳጅ ኤክስፖርቷን በሀገር ውስጥ የፓይፕላይን መስመር ወደ ቀይ ባሕሩ የያንቡ ወደብ አዙራው ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ቀይ ባሕር 7 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የኃይል አቅርቦት የሚሸከም በመሆኑ፣ በዚህ መስመር ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ንረትና ቀውስ ያስከትላል። ሪላድ ይሄንን ከኢራንና ከሁቲዎች የሚሰነዘረውን ስጋት በጥብቅና በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከታተለችው መሆኑ ተነግሯል።
በቀጠናው ያለውን ውጥረት ይበልጥ ያባባሰው፣ ሁቲዎች ሳዑዲ ዓረቢያ በእነሱ ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን አየር ማረፊያ በቦምብ ደብድባለች በሚል በመክሰስ፣ ባለፉት አራት ዓመታት የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ ባለፈው ሰኞ ወደ ሳዑዲ ግዛት ሚሳኤሎችን መተኮሳቸው ነው። ይህ አጠቃላይ ቀውስ የጀመረው ባለፈው የካቲት 28 ቀን እስራኤልና አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ቴህራን የዓለምን አንድ አምስተኛ የኃይል አቅርቦት የሚያስተላልፈውን የሆርሙዝ ስትሬት መዝጋቷን ተከትሎ እንደነበር ይታወሳል። በሰኔ ወር በቴህራንና በዋሽንግተን መካከል ተደርሶ የነበረው ደካማ የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረሱን ተከትሎ ቀውሱ ወደ ሙሉ ጦርነት የማደግ ስጋቱ እጅግ አይሏል።

21 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.