Logo
FastMereja
የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያዘጋጀው ታላቅ የሥራ ትስስር (Job Fair) ተካሄደ

​#fastmereja I የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በ2018 ዓ.ም ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ምሩቃንን እና ሌሎች የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን በቀጥታ ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማገናኘት ያለመ የመጀመሪያው የሥራ ትስስር (Job Fair) ዛሬ ሐምሌ 09 ቀን 2018 ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት አካሂዷል።

​የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተሾመ ፌይሳ ዋክቶሌ ለፋስት መረጃ በሰጡት ቃል እንደገለጹት፤ ይህ የሥራ አውደሪ የተዘጋጀው ቀጣሪ ኢንዱስትሪዎችንና ሥራ ፈላጊ ሰልጣኞችን በአንድ መድረክ በማገናኘት፣ ሁለቱም ወገኖች ተፈላጊ ሰራተኛና የሥራ ዕድል ፍለጋ የሚያባክኑትን ጊዜና እንግልት ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ኮሌጁ ይህንን መድረክ በተቋም ደረጃ ሲያዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በሌሎች መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና አማካሪዎች አማካኝነት ይዘጋጅ የነበረውን መርሃ ግብር ተቋሙ በባለቤትነት ተረክቦ ከተማ አቀፍ በሆነ መልኩ ማዘጋጀቱን አስረድተዋል።

​በአውደሪው ላይ የኮሌጁ 967 መደበኛና የአጭር ጊዜ ሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ 14ቱም ኮሌጆች ሰልጣኞቻቸውን ይዘው እንዲገኙ ጥሪ ተላልፎላቸዋል። ሰልጣኞቹ ከቀጣሪዎች ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ የሲቪ (CV) አጻጻፍ፣ የቃለ መጠይቅ ዝግጅት፣ አለባበስ እና የስራ ፈጠራ አስተሳሰብን በሚመለከት ሰፊ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይህ ዝግጅት ምሩቃኑ በራስ የመተማመን ስሜት ኖሯቸው ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ታምኖበታል።

​በዕለቱ በተካሄደው የሥራ አውደሪ ላይ ከሆቴል፣ ከኮንስትራክሽን፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከዘመናዊው የፈጠራ ግሪን ቴክኖሎጂ እና ከኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ዘርፎች የተውጣጡ ከ35 በላይ ኢንዱስትሪዎች ተገኝተው የቅጥር ሂደቶችን ሲያከናውኑ ውለዋል። ከተለመደው የቅጥር ሁኔታ በተጨማሪ በኮሌጁ በቴክኖሎጂ (ICT) ዘርፍ የተደራጁና የሰው ሰራሽ አስተዋጽኦ (AI) መተግበሪያዎችን በመጠቀም ድረ-ገጾችንና የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች የራሳቸውን ማሳያ ጥግ ይዘው ስራዎቻቸውን ለእይታ አቅርበዋል።

​ለአንድ ቀን ብቻ የሚቆየው ይህ የሥራ አውደሪ መርሃ ግብር፣ በቀጣይም በየዓመቱ ከምረቃ ሥነ-ሥርዓት አስቀድሞ በቋሚነትና በስፋት የሚዘጋጅ ዓመታዊ መርሃ ግብር ሆኖ እንደሚቀጥል ዋና ዲኑ አቶ ተሾመ ፌይሳ ጨምረው ገልጸዋል።
#ኹነት

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.