Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ባህል) የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የ2017 ዓ.ም የ"አምባሳደር አሸንዳ" ማዕረግ ተሸላሚ የነበረችውን ወጣት ዜማ እምብዛን ከክብር ማዕረጓ ማንሳቱን ያስታወቀበት ይፋዊ መግለጫ፣ በባህል ልማት ስም የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ተቋማትን ሚና እና የአስተሳሰብ አድማስ በድጋሚ በትዝብት መድረክ ላይ የሚጥል ሆኗል። ቢሮው ውሳኔውን ያስተላለፈው ወጣቷ «አሸንዳ ኢትዮጵያ» በሚል መጠሪያ ባህሉን ለማስተዋወቅ መሞከሯን እንደ ትልቅ ወንጀልና የሕዝብን እሴት የመጣስ ተግባር ቆጥሮት ነው። ይህ እርምጃ ባህላዊ ቅርሶችን ከማሳደግና ዓለም አቀፋዊ አድማሳቸውን ከማስፋት ይልቅ፣ ጥበብንና ባህልን በፖለቲካዊ ቅጥሮች ውስጥ የመሸበብ አደገኛ ዝንባሌ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

አሸንዳ ዕድሜ ጠገብ የሆነ፣ የማንነት፣ የነጻነትና የሴቶች ክብር መገለጫ የሆነ እምቅ የሕዝብ ቅርስ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ የማስተዋወቅ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም፣ ዋና ዓላማው ቅርሱ ከክልላዊ ወሰን አልፎ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ፣ አልፎ ተርፎም በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲመዘገብ መሥራት መሆን ነበረበት። ሆኖም ግን፣ወጣቷ አምባሳደር የቅርሱን አድማስ ለማስፋት እና ከሌሎች ወገኖች ጋር ድልድይ ለመፍጠር «ኢትዮጵያ» የሚለውን ስም በማካተቷ ብቻ ማዕረጓን መንጠቅ፣ ከተቋማዊ ራዕይ ማነስ እና ባህልን የፖለቲካ ፍጆታ ከማድረግ የሚመነጭ እጅግ ጠባብ አካሄድ ነው።

የባህልና ቱሪዝም ቢሮው በመግለጫው ላይ ወጣቷን «የሕዝቡን ባህላዊ እሴቶች የማይወክል ተግባር ፈጽማለች» ሲል ቢከስም... በተግባር ግን ራሱ ቢሮው የትኛውን ባህላዊ እሴት እየጠበቀ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ባህል የሰዎች መገናኛ፣ የፍቅርና የሰላም መድረክ እንጂ ሰዎችን ማግለያና መቅጫ መሣሪያ አይደለም። ወጣት ዜማ እምብዛ ለአሸንዳ በዓል ሰፊ ዕውቅና ለመስጠት ያሳየችውን ተነሳሽነት በበጎነት ከመደገፍና ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን ከመምራት ይልቅ፣ እንደ ፖለቲካ ወንጀለኛ ቆጥሮ በይፋ ማዋረድና ማዕረግ መንሳት፣ በክልሉ ጥበብና ባህል ላይ የተጣለ ትልቅ ጥላሸት ነው።

ይህ ክስተት የሚያሳየው ትልቁ እውነት፣ የታሪክና የባህል ተቋማት ከዘመኑ የፖለቲካ ውጥረት እና ከልሂቃኑ መከፋፈል ራሳቸውን ማላቀቅ አለመቻላቸውን ነው። የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህንን መሰል የተሳሳተ ውሳኔ በማሳለፍ... አሸንዳን ለዓለም ከማስተዋወቅ ይልቅ በጠበበ የፖለቲካ አጥር ውስጥ መልሶ አግቷታል። ተቋማት የሕዝብን ውብ ባህል ወደ ኋላ ከመጎተት እና በወጣቶች የፈጠራ አቅም ላይ ሳንሱር ከመጣል ተቆጥበው፣ ጥበብ ያለ አንዳች የድንበር ገደብ እንድታብብ የነጻነት አየር ሊፈጥሩላት ይገባል የሚለው የብዙኃኑ ጥያቄና የዚህ ክስተት ዋነኛ ማሳያ ነው።

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.