Logo
Getu Temesgen
ወልቂጤ : የመሐመድ ናስር ታሎር (MNT) የታዳጊዎች እግር ኳስ አካዳሚ
#ethiopia | ወልቂጤ — በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው የ"መሐመድ ናስር ታሎር" (MNT) የታዳጊዎች እግር ኳስ አካዳሚ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ረገድ ተስፋ ሰጪና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን አርአያነት ያለው ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰይፈ ዓለሙን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ የሚገኙ የስፖርት ሥልጠና ፕሮጀክቶችን በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል።

የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ንቅናቄና የተተኪዎች ሥልጠና*

የቢሮ ምክትል ኃላፊው አቶ ሰይፈ ዓለሙ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በክረምት ወቅት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ በሁሉም ዞኖች በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የታጀቡ ሥራዎችን የማስጀመር ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።

በክረምት ወቅት ታዳጊዎች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ በማድረግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያሳልፉ ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው፤ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለመፍጠር በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ የንቅናቄ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሰርከስ ሰልጣኞችን እየመለመለ እንደሚገኝና በ2019 በጀት ዓመት የክልሉን የሰርከስ ቡድን በአንድ የስልጠና ማዕከል ሰብስቦ ሥራ ለማስጀመር ማቀዱን አስታውቀዋል።

በወልቂጤ ከተማ በተደረገው ምልከታ ቡድኑ እጅግ መደሰቱን የገለጹት አቶ ሰይፈ፤ በተለይም በእግር ኳስ በየዕድሜ ክልሉ የሚሰጠው ሥልጠና ጠንካራና የአሰልጣኞችን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማው የሚገኘው የMNT እግር ኳስ አካዳሚ በተተኪ ታዳጊዎች ላይ እየሠራ ያለው ሥራ ለሀገርና ለክልሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፣ በዞኑ የሚገኙ ባለሀብቶች ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር በመከተል ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የማኅበረሰብ ድጋፍ**
የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ሽኩር በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ክረምት ወጣቶችን በማስተባበር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣቶችና ታዳጊዎች በአካባቢ ጽዳት፣ በችግኝ ተከላ፣ በኪነ-ጥበብ እና በስፖርታዊ ውድድሮች እንዲሳተፉ እየተደረገ ከመሆኑም በላይ፤ አቅመ-ደካሞችን የመደገፍና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ደብተር የማሰባሰብ ሥራዎች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ስለ መሐመድ ናስር ታሎር (MNT) አካዳሚ

የአካዳሚው አሰልጣኝና ሥራ አስኪያጅ አብድልህኒ ተሰማ እንደገለጹት፤ አካዳሚው በአሜሪካ ሀገር በሚኖረውና የከተማው ተወላጅ በሆነው በአቶ መሐመድ ናስር የተመሠረተ ነው።

ከተመሠረተ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ አካዳሚ፦

* ከ6 እስከ 18 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን ያቅፋል።

* በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ ታዳጊ ስፖርተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል።

የጉራጌ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን

21 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.