Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በመጪው እሁድ በሚደረገው የ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ለሁለተኛው አጋማሽ እስኪመለሱ የሚኖረው የእረፍት ሰዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ ከ20 እስከ 25 ደቂቃ ሊረዝም እንደሚችል ተጠቆመ።

ይህ ሊሆን የቻለው በኒው ዮርክ ኒው ጀርሲ ስታዲየም በሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ እረፍት ወቅት፣ ልክ እንደ አሜሪካው 'ሱፐር ቦውል' አይነት የ11 ደቂቃ ግዙፍ የሙዚቃ ትዕይንት ለማቅረብ በመታቀዱ ነው።

በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ቦርድ የጨዋታ ህግ መሰረት፣ ተጫዋቾች የሚያገኙት የእረፍት ሰዓት "ከ15 ደቂቃ መብለጥ የለበትም" የሚል ደንብ አለ። ይሁን እንጂ የዓለም እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ፊፋ (FIFA) ውስጥ ያሉ ምንጮች እንደገለጹት፣ በእሁዱ ጨዋታ የእረፍቱ ጊዜ 20 ደቂቃ አካባቢ ይሆናል። አሁን ላይ ባለው አንዱ አማራጭ መደበኛውን የ15 ደቂቃ እረፍት ሰጥቶ፣ የታቀደውን የ11 ደቂቃ የሙዚቃ ትዕይንት ማካሄድ ነው።

ፊፋ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ዓመት በኒው ጀርሲ በተካሄደው የዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ኮልድፕሌይ፣ ጄ ባልቪን፣ ዶጃ ካት፣ ቴምስ እና ኢማኑኤል ኬሊ ያቀረቡትን ትዕይንት ተከትሎ፣ የእረፍት ሰዓቱ በአጠቃላይ 24 ደቂቃ መፍጀቱ ይታወሳል።

ለእሁዱ ትልቅ የፍጻሜ ጨዋታ እረፍት በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ታዋቂዎቹ ድምጻውያን ማዶና፣ ሻኪራ እና የኮሪያው ታዋቂ የሙዚቃ ቡድን ቢቲኤስ በዋና አቅራቢነት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ጃስቲን ቢበርም በዝግጅቱ ላይ እንዲሳተፍ ተጋብዟል።
በተጨማሪም በርና ቦይ፣ ጉስታቮ ዱዳሜል እና የፒኤስ22 ቾረስ ከኮልድፕሌይ ጋር በመሆን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። አጠቃላይ ዝግጅቱን ያቀናበረው ደግሞ የኮልድፕሌይ ድምጻዊ ክሪስ ማርቲን ነው።

የዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ በአካባቢው አቆጣጠር ከቀኑ 9:00 ሰዓት (በለንደን አቆጣጠር 8:00 ምሽት) ላይ የሚጀምር ሲሆን፣ ከዚያ አስቀድሞ ከቀኑ 7:30 ሰዓት (በለንደን 6:30 ምሽት) ጀምሮ ደማቅ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ይካሄዳል።

በዚህ ታላቅ የመዝጊያ መርሃ-ግብር ላይ ተዋናይ ቶም ክሩዝ፣ ላውራ ፓውሲኒ፣ ኒኮል ሸርዚንገር፣ ሮቢ ዊሊያምስ እና ታዋቂው ዩቲዩበር አይሾው ስፒድ የሚሳተፉ ሲሆን፣ የአሜሪካን ብሔራዊ መዝሙር ደግሞ ጄኒፈር ሁድሰን እንደምትዘምረው ታውቋል።

ስፔን ዛሬ በዳላስ በተደረገው የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይን 2 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው ማለፏን ያረጋገጠች ሲሆን፤ ረ ነገ በአትላንታ ከሚገናኙት እንግሊዝ ወይም አርጀንቲና መካከል አሸናፊውን በእሁዱ ታላቅ ፍጻሜ የምትገጥም ይሆናል።

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.