Logo
EBC
ከኃይል ፖለቲካ ወደ ብስለት፡ አዲሱ የሀገራዊ መግባባት መሠረት
******************

(የዕለቱ መልዕክት)

የኃይል እና ጠመንጃ ፖለቲካ አማራጭ ወደ ኋላ ከማስቀረት ባለፈ ያተረፈልን ዘላቂ ሰላም የለም።

ዛሬ ላይ የቆምንበት ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየን ትልቁ እውነት፣ በጉልበት የራስን ፍላጎት በሌላው ላይ የመጫን ያለፈበት አካሄድ ሀገርን ከማድማትና ትውልድን ከመገበር ውጪ የፈወሰው አንዳችም ማህበራዊ ጠባሳ አለመኖሩን ነው።

አሁን ግን ይህንን አውዳሚ የፖለቲካ ባህል በአዲስ የማህበረሰባዊ ንቃትና በሃሳብ ልዕልና የምንተካበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

የሃሳብ ልዕልና ማለት የሀሳብ ድህነትን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመሸፈን መሞከርን በበሰለ የፖለቲካ ክርክር ማሸነፍ መቻል ማለት ነው።

ሀገራዊ ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት ከጦር ሜዳ ይልቅ በሃሳብ አውድማ ላይ መፋለም፣ የተሸናፊና አሸናፊ ሳይሆን የጋራ ድልን የሚያረጋግጥ ብቸኛው ስልጣኔ ነው።

ይህንን ሽግግር እውን ለማድረግ ደግሞ ይቅርታን እና ምክክርን ማዕከል ያደረገ አዲስ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር የቆዩ የፖለቲካ ቂሞችን በይቅርታ የምንተካበት፣ የታሪክ ስብራቶቻችንን የምንጠግንበት እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ ምክክር የምንፈታበት ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኖ ቀርቧል።

ይህ መድረክ ተራ የፖለቲካ ድርድር ወይም የጊዜያዊ ስምምነት መፍጠሪያ ሳይሆን የኢትዮጵያን የወደፊት የጋራ እጣ ፈንታ በአዲስ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል የለውጥ አጋዥ መሣሪያ ነው።

ቂምን ማስተናገድና ያለፈን የታሪክ ቁርሾ ዛሬ ላይ እያደሱ መቀጠል ሀገርን ወደማያልቅ አዙሪት ውስጥ ከመክተት ባለፈ ትርፍ የለውም።

በመሆኑም ይህንን የታሪክ አጋጣሚ በመጠቀም ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት፣ እርስ በርስ በመደማመጥና በመቻቻል አዲሷን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል።

ጠመንጃን አስቀምጦ በሃሳብ መነጋገር መቻል የድክመት ሳይሆን የላቀ የፖለቲካ ብስለትና የሀገር ተቆርቋሪነት መገለጫ ነው፤ የዛሬው ምርጫችንና ትውልዳዊ ኃላፊነታችንም ይሄው ሊሆን ይገባል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

25 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.