Logo
EBC
ዓለም አቀፉ የፓርላማ፣ መረጃና ደህንነት ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ
**************

ዓለም አቀፉ የፓርላማ፣ መረጃና ደህንነት ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። ፎረሙ በአፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን አዲስ አበባም መድረኩን በማስተናገድ ሁለተኛዋ የአፍሪካ ከተማ ሆናለች።

ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ ሽብርተኝነትን መከላከል፣ ቀጣናዊ ፀጥታ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በዋናነት ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ፎረም የምታስተናግደው 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ መልኩ ባካሄደች ማግሥት መሆኑ ልዩ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

አፈ ጉባኤው አክለውም፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና በቆራጥነት ለመከላከል ሀገራችን ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍም ኢትዮጵያ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ያብራሩት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የዲጂታልና የሳይበር ደህንነት ይበልጥ የተጠበቀ እንዲሆን በየጊዜው ከሚፈጠሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ጋር ራስን በማላመድ ረገድ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ለጉባኤው ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪንግ ማሲንጋ በበኩላቸው፣ ይህ ፎረም ሀገራት መረጃዎችን የጋራ በማድረግ የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፣ መሰል ዓለም አቀፍ የደህንነት ትብብሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የፎረሙ ሊቀመንበር ሮበርት ፒትንገር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና ሌሎች ቀጣናዊ የፀጥታ ስጋቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ "እውነተኛ አጋር" መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ ሀገር ናት ሲሉ ገልጸዋል።

በሳደት መሀመድሳኒ
#ethiopianbroadcastingcorporation #parliamentaryintelligencesecurityforum #pisf2026 #securityforumafrica

26 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.