Logo
Getu Temesgen
የኢትዮጵያ ንግድ ማህበር አይነትና ባህርያት ፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትርጉም እና ባለ አንድ አባል የንግድ ማህበር ህጋዊ አስፈላጊነት

አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ አዋጅ ቁጥር 1243/13
መግቢያ
#ethiopia | ሰዎች በንግድ ስራ ለመሰማራት በህብረት ገንዘብ እውቀት ሙያ ንብረት ጉልበታቸውን በማወጣት ተደራጅተው ከሚገኘዉ ትርፍ ተካፋይ ለመሆን ህጋዊ መስፍርታቸውን በመጠበቅ ተቀባይነት ያለው የንግድ ማህበር ያቋቁማሉ። በዚህ አጭር ጽሁፍ አጠቃላይ የንግድ ማህበራትን በህጉ የተካተቱን በመጥቀስ ባአይነት ፣ባህርያታቸውን፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ምን እንደሆነ ፣ እንዲሁም ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ህጋዊ አስፈላጊነትን በመዘርዘር ለእናንተ እናቀርባለን።

1. የንግድ ማኅህበራት ጽንሰ ሀሳብ በኢፊድሪ ህገመንግስት...

ሰወች በግልም በሆነ በህብረት የንግድ ስራን የመስራት መብት በኢፊድሪ ህገ መንግስት በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ የንግድ አዋጅ ሆነ በሌሎች አግባብነት ያላቸው አዋጆች የተሰጠ መብት ነው። የንግድ ስራዎችን ለመስራት የመደራጀት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 31 ላይ ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማህበር የመደራጀት መብትን የሚፈቅድ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ በንግድ ማህበራት የመደራጀት መብት በህገመንግስቱ አንቀፅ 41(2) “ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደርያውን ስራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው” ከሚለው ህገ-መንግስታዊ መብት አንፃር ያየነው እንደሆነም ዜጎች አዋጪ ነው ባሉት የንግድ ማህበር መርጠው እንደ መተዳደርያ ስራቸው ሊወስዱት የሚያስችል ህገመንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑን በቀላሉ መረዳት የሚቻል ነው።

2. የንግድ ማህበራት አይነቶች በአዲሱ ንግድ ህግ አዋጅ ቁጥር 1243/13

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 174 መሰረት በእኛ ሀገር ሰባት ዓይነት የንግድ ማኅበራት አሉ፡፡ እነሱም፡-
• የኅብረት ሽርክና ማኅበር / General Partnership/
• ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር /Limited Partnership/
• ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር /Limited Liability Partnership/
• የአሽሙር ማህበር /Joint Ventur/
• የአክሲዮን ማህበር /Share Company/
• ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /Private Limited Company/ እና
• ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር / One Person private limited Company/ ናቸው፡፡
2 የእያንዳንዱ ንግድ ማህበራት ባህሪይ በአዲሱ ንግድ ህግ ....

2.1. የኅብረት ሽርክና ማህበር

የህብረት ሽርክና ማህበር በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 283 መሰረት ማኅበርተኞች እያንዳንዳቸው ባንድነትና ሳይከፋፈል እርስ በርሳቸውና ለማህበሩ ግዴታዎች አላፊዎች የሚሆኑበት ማኅበር ነው፡፡ ይህም ማለት ማህበሩ ለሚያጋጥመው አደጋ ወይም እዳ ሁሉ እያንዳንዱ አባል በግሉ፣ ወይም ሁሉም በአንድነት ወይም ከሁሉም የተወሰኑት ብቻ በተናጥል ለእዳው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ማንኛዉም ተቃራኒ ስምምነት ሦስተኛ ወገኖችን መቃወሚያ ሊሆን አይችልም፡፡

2.2. ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር....

ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማኅበር ከስሙ እንደምንረዳው የማኅበርተኞቹ ኃላፊነት የተለያየ የሆነበት ማኅበር ነዉ፡፡ እነሱም ኃላፊነታቸዉ ያልተወሰነ ሸሪኮችና ኃላፊነታቸዉ የተወሰነ ሸሪኮች ናቸው፡፡ በአዲሱ የንግድ ህግ አንቀጽ 212 መሰረት ኃላፊነታቸው ያልተወሰነ ሸሪኮች የሚባሉት ለማኅበሩ ግዴታዎች በሙሉ ከማኅበሩ ጋር በአንድነትና በተናጠል ኃላፊነት ያለባቸዉ ሲሆን ኃላፊነታቸዉ የተወሰነ ሸሪኮች ደግሞ መዋጮ ለማድረግ ቃል በገቡት መጠን ብቻ ለማኅበሩ ግዴታች ኃላፊ የሚሆኑ ናቸዉ፡፡ ኃላፊነታቸው የተወሰነ ሸሪኮች በወክልናም ሆነ በሌላ በማንኛዉም ሁኔታ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ መሆን አይችሉም፡፡

2.3 ኃላፊነታቸው የተወሰነ የሙያ ሽርክና ማኅበራት ....

በአዲሱ የንግድ ህግ ውስጥ ከተካተቱ ጉልህ ለውጦች መካከል አንዱ የሆነው ይህ አዲስ የሽርክና ማህበር አይነት፣ ሰዎች በተለይም የሙያ ስራዎችን ለመስራት በሙያ ከሚመስሏቸው ሌሎች ሰዎችና ለሙያው ደጋፊ የሆነ አገልግሎት ሊሰጡ ከሚችሉ አጋሮቻቸው ጋር ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሆነው የሚያቋቁሙት እና ኃላፊነቱም በሽርክና ማኅበሩ ሃብት ላይ ብቻ የተወሰነ የንግድ ማኅበር ነው።

2.4 የአሽሙር ማህበር....

የአሽሙር ማህበር ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በመካከላቸዉ በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት የሚያቋቁሙት ሲሆን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በጽሁፍ መረጋገጥና በሌሎች የንግድ ማህበሮች የተደነገጉ የማስመዝገብ ሰርዓቶች የማይፈፀሙበት፣ የሕግ ሰዉነት የሌለውና በሶስተኛ ወገኖች ዘንድ የማይታወቅ መሆኑ ሲሆን ከታወቀ ግን እንደ ሕብረት ሽርክና ማህበር እንደሚቆጠር ሊታወቅ ይገባል፡፡

2.5 የአክሲዮን ማህበር...

የአክሲዮን ማህበር ማለት በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 245 መሰረት ዋናው ገንዘቡ ወይም ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክስዮን የተከፋፈለና ኃላፊነቱ በማኅበሩ ሀብት ብቻ የተወሰነ (ለዕዳው ንብረቱ ብቻ ዋስ የሆነ) ማኅበር ነው፡፡

2.6 ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር...

በአዲሱ የንግድ ሕግ አንቀጽ 495 መሰረት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማለት ዋና ገንዘቡ በሙሉ አስቀድሞ የተከፈለ፣ በአክስዮን የተከፈለ እና ባለአክስዮኖች መዋጮቸዉን ገቢ እስካደረጉ ድረስ ለማኅበሩ ዕዳ ኃላፊ የማይሆኑበት የንግድ ማኅበር ነዉ፡፡

2.7 ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ...

ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማለት አንድ ሰዉ በግሉ በሚሰጠዉ መግለጫ መሰረት የተቋቋመ የንግድ ማኅበር ነዉ፡፡ ማኅበሩ ከአባሉ የተለየና የተነጠለ የራሱ የሕግ ሰዉነት አለዉ፡፡ አባሉ የራሱን መወጮ ሙሉ በሙሉ እስከ ከፈለ ድረስ ማኅበሩ ላይ ለሚፈለገዉ ዕዳ በግሉ አይጠየቅም፡፡ የማኅበሩ ዝቅተኛ ዋና ገንዘብ ከ ብር አስራ አምስት ሺህ ማነስ የለበትም፡፡ ማኅበሩን ለማቋቋም አባሉ የሚሰጠዉ መግለጫ ሰነዶችን ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠዉ አካል ፊት መደረግ አለበት፡፡ መግለጫዉም በንግድ መዝገብ ዉስጥ መግባት አለበት፡፡ ግለሰብ ነጋዴ የንግድ ሥራዉን ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርነት መለወጥ ይችላል፡፡

2.8 ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወደ ባለ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚቀየርበት ምክንያት...

ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአክስዮን አባላቱ እየቀነሱ በመምጣት ወደ አንድ ዝቅ ካለ እና በስድስት ወር ጊዜ ዉስጥ ሌላ ሰዉ ካልገባ ማኅበሩ የሚፈርስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ካልሆነ የባለአክስዮኖቹ ቁጥር ወደ አንድ ዝቅ ካለበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ዉስጥ የመመስራቻ ጽሁፉን በማሻሻል ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አድርጎ ማስመዝገብ ይቻላል።

2.9 ባለ አንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአዲሱ ማህበር የተካተተበት ዋና አላማ...

ይህ ማህበር በአዲሱ ንግድ የተካተተ ሲሆን ግለሰቦች የንግድ ስራቸውን ሲያከናውኑ ከራሳቸው ከግላቸው ሀብት በመነጠል የሚያቋቁሙት ማህበር በእዳም ቢሆን በህግ ጉዳዮች ክንውኖች የራሱን ጉዳይ ራሱ ማህበሩ ህጋዊ ሰውነት ኖሮት ህጋዊ የነሰግድ ስራዎችን የሚያንቀሳቅስ ነው።

በመጀመሪያው ንግድ ህግ ይህ ማህበር ባለመኖሩ ባለሀብቶች ይህን እድል መጠቀም አልቻሉም በቀድሞው ህግ ይህ ባለ አንድ ማህበር ስለሌለ ለቁጥር ብቻ አባሉ ከሁለት በላይ እንዲሆን ዘመዱን ቤተሰቡን አስገብቶ ሀብቱ የራሱ ብቻ ነገር ግን ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰወች እንደ ተመሠረተ በማድረግ ማህበሩ የሚመሰረት ሲሆን አለመግባባት ሲፈጠር ባለሀብት እንደፈለገ መምራት ያስቸግረዋል። በአዲሱ የንግድ ህግ ግን ይህ ማህበር በመፈቀዱ በአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መቋቋም በህግ መፈቀዱ ለባለሀብቶች ወሳኝነት ያለው ሲሆን ለንግድ እንቅሰቃሴው ከፍተኛ በርን የሚከፍት ነው።

ግለሰብ ነጋዴ የንግድ ሥራዉን ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርነት መለወጥ ይችላል፡፡ ሌላው ግለሰብ ነጋዴዎችም ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግለሰብ ማኅበር ለመመስረት እና ባለ አንድ ማህበር መስረተው ንግዳቸውን እንዲያንቀሳቅሱ የሚረዳ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ ቀድሞ ለነበረበት ማህበር ከመሆኑ በፊት በግለሰብ ደረጃ ቀድሞ ለነበረበት ለግለሰብ ንግድ ስራ ለገባበት ዕዳ ሁሉ ከማኅበሩ ጋር በአንድነት እና በተናጠል ኃላፊ ነዉ፡፡
የተፈቀደ ሲሆን ይህ ለባለሀብቶች ትልቅ የንግድ
መስመር ነው።

3. ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ የንግድ ማህበር የተለያየ አይነት የንግድ ማህበራት የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ለተፈለገው የንግድ አለማ የትኛው እንደ ሚሻል የንግድ ህግ ባለሙያ በማማከር አስፈላጊ ነው የሚባለውን ማህበር እንደ ንግዱ አይነት ለመመስረት የሚያስፈልገውን መስፈርት በሟሟላት መመስረት የሚቻል ሲሆን ባለአነድ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም በአንድ ሰው የሚመሰረት ራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው ሲሆን ለማህበሩ አጠቃላይ ኃላፊነቱን ራሱ ማህበሩ የሚወስድ መሆኑን በዚህ አስፍረናል። ዋናው የዚህ ጹሁፍ ዋና አላማ የንግድ ማህበር አይነቶችን ምን እንደሚመስሉ ከህግ አንጻር ለእናንተ ለማሳወቅ ነው።

https://www.facebook.com/s...
https://t.me/Fantahunlawye...
tiktok.com/fantahun62395
0929101037

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.