Logo
Getu Temesgen
"E.V.A.G.N" የኢትዮጵያ ሠዓሊያንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስተዋውቅ ነው
#ethiopia | የኢትዮጵያን የሥነ-ጥበብ አድማስ ለማስፋትና የሠዓልያንን የፈጠራ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው "Ethiopian Visual Arts Global Network" (E.V.A.G.N) የተሰኘው ግዙፍ የመረጃ ቋት (Database) የማስተዋወቂያ ፕሮግራም ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በሐገር ውስጥ የሚገኙ ሠዓሊያን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተካሄደ።

ይህን ለአንድ ዓመት ያህል ሲደራጅ የቆየውን የመረጃ ቋት ያዘጋጀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው **የአለ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት** ነው።

ከስነ-ስርዓቱ የተደመጡ ንግግሮች

አቶ አገኝሁ አዳነ
(የአለ የሥነጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ዳይሬክተር):
ፕሮግራሙን በይፋ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፣ ይህ ግዙፍ የመረጃ ቋት ለኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን እጅግ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው። የሥነጥበብ ትምህርት ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስፈልገውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን:
የዚህ ኔትወርክ እውን መሆን ለሥነጥበብ ባለሙያው ዓለም ዛሬ በደረሰበት የቴክኖሎጂ አማካኝነት በየትኛውም የዓለም ክፍል ከሚገኝ ባለሙያና መሰል የትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር እንዲሁም ሥራዎቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያስተዋውቅ ትልቅ በር የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህ ኔትወርክ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በቴክኖሎጂ ለማገናኘት ትልቅ ድልድይ ነው::"

የቴክኖሎጂው በስተጀርባ እና አስተዋጽዖ አበርካቾች
ይህንን ዘመናዊ የመረጃ ቋት የገነባው በትምህርት ዘርፍ፣ በሶፍትዌርና ሃርድዌር ቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና ማማከር ላይ የተሰማራውና መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገው "INFNOVA Technologies" የተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ልደቱ ታደሰ ስለ መረጃ ቋቱ ጠቀሜታና እስከ አሁን ስለተከናወኑት ሥራዎች ዝርዝር ማብራሪያ ለታዳሚው የሰጡ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ከአለ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ጋር በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል ሲያስተባብሩ የነበሩት ሠዓሊ ሳምሶን መረሳ በበኩላቸው፣ ለሥራው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ ግለሰቦችን በሙሉ አመስግነዋል።

በተጨማሪም በጀርመን አገር የሚኖረው **ሠዓሊ ግርማቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን በድምፅ ለታዳሚው አስተላልፏል።

የሠዓሊያን ምዝገባና ጥሪ
የመረጃ ቋቱ ይፋ ከተደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ በርካታ የሐገር ውስጥና የውጭ አገር ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያን ኔትወርኩን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ እስከ አሁን ከሁለት መቶ (200) በላይ ባለሙያዎች ምዝገባ አከናውነዋል።

በማስተዋወቂያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ሠዓሊያንም በሙሉ በዕለቱ የኔትወርኩ አካል ሆነዋል።

በትምህርት ቤቱ አስተባባሪዎች የቀረበው ጥሪ እንደሚያመለክተው፦

* በሐገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ የአለ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ምሩቃን፣

* በሌሎች ተቋማት የሠለጠኑ ባለሙያዎች፣ እና

* የልምድ ሠዓሊያን በሙሉ፣

ማንነታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን የሚገልጽ መሠረታዊ መረጃቸውን ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን ወይም የተዘጋጀውን ባርኮድ ስካን በማድረግ ቅጹን እንዲሞሉና የዚህ ዓለም አቀፍ መረብ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

የምዝገባ ቅጽ ሊንክ: https://forms.gle/gWHXpKub...
#በይትባረክ ዋለልኝ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.