Logo
FBC
እንደገና የተወለደው ቀበና…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

በ87 ነጥብ 6 ሔክታር መሬት ያረፈው እና 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ፕሮጀክቱ የወንዝ መከላከያ ግንቦችን፣ ዘመናዊ ድልድዮችን እና ሰፊ አረንጓዴ ሥፍራዎችን ይዟል።

ይህ ቀበናን ውብ ገጽታ ያለበሰው እና የትውልድ ዐሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ነዋሪዎቿን አስደስቷል።

የቀበና ነዋሪዎቹ አቶ አለማየሁ፣ አቶ አወቀ እና ወ/ሮ መሰሉ ስለ ቀበና ልማት ድሮና ዘንድሮን እያነሱ ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

አቶ አወቀ÷ የነዋሪው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ንጹህ የነበረው የቀበና ወንዝ እየተበከለ እና የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ እየተለቀቀበት ቀድሞ የነበረውን ውበትና ገፅታውን እንዳጣ ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለነዋሪው የማይመች እና ጤናን የሚነሳ ሆነ ይላሉ፡፡

ቀበና አካባቢ ተወልደው ላለፉት 49 ዓመታት የኖሩት ወ/ሮ መሰሉ በበኩላቸው÷ የቀበና የቀድሞ ገፅታ በጫካ የተሸፈነ መሆኑን ይናገራሉ። በቀበና ወንዝ ቅዳሜ እና እሑድ ልጆች ጊዜያቸውን በዋና እና ሌሎች ጨዋታዎች የሚያሳልፉበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በሒደትም ቦታው መበከሉንና ለመዋኘት ቀርቶ ለማየት ደስ ወደማይል ገጽታ መቀየሩን ነው የሚያስረዱት፡፡

ሌላው የቀበና ነዋሪ አቶ አለማየሁ በ1959 ዓ.ም ነው በቀበና የተወለዱት፡፡ ስለአከባቢውም ብዙ ትዝታ አላቸው፡፡ መንገዱ አስቸጋሪ ስለነበር እና በአንድ ወቅት አዳልጧቸው ቀበና ወንዝ ውስጥ በመግባታቸው ከስራ እንደቀሩ ያስታውሳሉ፡፡ አሁን ያ ሁሉ ተለውጦ እንዲህ ተውቦ በማየታቸው "ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለሁ" ይላሉ፡፡

"ቀደምት ሰዎች እኔ ያየሁትን ቢያዩ" ሲሉ ቁጭታቸውን የገለፁት ነዋሪው በተወለዱበት ቦታ ላይ በአሁኑ ወቅት ውብ የህጻናት መጫወቻ መሰራቱን በማየታቸው እንደተደሰቱ ተናግረዋል። አቶ አለማየሁ በዚህ ምክንያት "አባቴ እዛ ቦታ ላይ ሐውልት እንደተሰራለት እቆጥረዋለሁ" ሲሉም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ መሰሉ በተሰራው ልማት የቀበና ገጽታ ተለውጦ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው÷ ልጆች እና ወጣቶች ምቹና ጤናማ በሆነ አካባቢ እንዲያድጉ ያስችላል ብለዋል፡፡

በልማቱ ቀበና ውበት መላበሷ እንዳስደሰታቸው የሚናገሩት አቶ አወቀ÷ የአካባቢው ማሕበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ በመሆኑ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ቀበና ድምጻዊ ጸሀዬ ዮሐንስ የተወለደባት፣ የቦረቀባት፣ የዋኘባትና ያዜመላት መሆኗን የገለጹት አቶ አወቀ÷ "ጸሐዬ ቀበና ላይ የሙዚቃ ድግስ አዘጋጅቶ ቀበናን ቀበና ማሰኘት አለበት" ነው ያሉት፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

የቀበና ነዋሪዎች ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ https://youtube.com/watch?...

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.