Logo
FBC
ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?

የነገዋን ኢትዮጵያ በጽኑ መሠረት ላይ የማቆም ሉዓላዊ ጉዞ ...

የቅኝ ገዢዎች የአፍሪካን ሕዝቦችን ለማንበርከክ የተጠቀሙበት ዋነኛ መሣሪያ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦችን በመከፋፈል የመግዛት ስትራቴጂ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለዘመናት የዘለቀ ትልቅ ማኅበራዊ ስብራትና ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

በኢትዮጵያ ላይም ተመሳሳይ የሆነ ሴራ በመስራት ለመከፋፈል የተሞከረ ቢሆንም፤ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለሺህ ዓመታት ጠንቅቃ የምታውቀው ኢትዮጵያ ልጆች በጠላት ሴራ ሳይከፋፈሉ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አድርገው በአንድነት በመቆም ሀገራቸውን የነጻነትና የጥቁር ሕዝቦች የትግል ተምሳሌት እንድትሆን አድርገዋል።

በዚህም የአፍሪካ የነጻነት እና የአንድነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ የጋራ ማንነትን የሚያጠናክር፣ ወንድማማችነትን የሚያጎለብት አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት ላይ ትገኛለች።

በዚህ ሂደት የመደመር እሳቤ የተለያዩ አቅሞችንና እሴቶችን ለጋራ ዓላማ ለማሰባብሰብ እንዲሁም የሀገር ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር እንደ ሁነኛ መፍትሔ እያገለገለ ይገኛል።

ይህ እሳቤ አቅምን ከመበተን ይልቅ፣ ሀገራዊ ጸጋዎችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የጋራ ራዕይን የማሳካት ዓላማ ያለው ሲሆን፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበርና በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና ለማጎልበት ወሳኝ መሠረት ነው።

የመደመር መንገድ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ፣ ዘላቂ፣ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በታሪክና በፖለቲካዊ አመለካከቶች ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን በሰለጠነ ውይይት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በታሪክ፣ በፖለቲካና በሀገራዊ ምልክቶች ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የመደማመጥ ባሕልን እያጠናከረ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የጋራ ማንነትን በተጨባጭ ለመግለጽ የሚያስችሉ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ታላላቅ ማዕከላት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የጋራ የነፃነትና የድል ታሪክ የሚያወሱ ፕሮጀክቶች መገንባት የብሔረሰቦችን ባህልና ሥልጣኔ በአንድ ጥላ ሥር በማምጣት hገራዊ ኩራትንና ትስስርን የሚያጎለብት ስራ ተሰርቷል።

እንዲሁም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ጭምር ተማሪዎች ስለ መላው ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶችና ታሪካዊ ትስስሮች እንዲማሩ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

የጋራ ትርክት ግንባታ ከውስጥ ሰላም ባለፈ ከሀገራዊ ሕልውና እና ከጂኦፖለቲካዊ ጥንካሬ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ አሰባሳቢ ትርክቶችን እንደ ትልቅ መሣሪያ በመጠቀም የብሔራዊ ጥቅም ማጠንጠኛዎችን የሚያስከብርና በሉዓላዊነት ጉዳይ የማይደራደር ዜጋ ለመቅረጽ እየተሰራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የጋራ ማንነትን የማጠናከር ሥራዎች ልዩነቶችን ውበት አድርጎ በመውሰድ ጠንካራ አንድነት ያለው በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው።

በመሆኑም የወደፊቱን ሀገራዊ ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ያለፉትን ስኬቶች ማጉላትና የጋራ ትርክትን ማሳደግ የእያንዳንዱ ዜጋ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የምሁራን ኃላፊነት ሆኖ ይቀጥላል።

አሰባሳቢና ገዢ ትርክት ለማስረጽ የሚዲያ፣ የኮሙኒኬሽንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ሲሆን፤ አብሮነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን መቅረጽ እንዲሁም አፍራሽ የትርክት ጫናዎችን በእውቀትና በእውነት መመከት ይገባል።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.