Logo
FBC
ገበታ ለትውልድ የኢትዮጵያን ደም ግባት የገለጠ ፕሮጀክት ...

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት፣ አነሳሽነትና አስተባባሪነት የተመሩት የገበታ ለትውልድ፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ድብቅ ውበት እያወጡ ደም ግባቷን እየገለጡ ለቱሪዝም እድገት ትልቅ የታሪክ እጥፋት የሚሆን አበርክቶን እየለገሱ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎቿን ውበት እያለበሰች የጎደሉ መሰረተ ልማቶችንም እያሟላች ለዜጎቿም ሆነ ከውጭ መጥተው ለሚጎበኟት እየደመቀች ትገኛለች፡፡

ይህም ግንባር ቀደም የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን ለምታደርገው ጥረት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ባስመዘገበቻቸው 19 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶቿ በአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ እነዚህ ሀብቶቿ የቱሪዝም አቅምን ጨምረው ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የውጭ ምንዛሪን ከመሳብ ባሻገር በየአካባቢዎቹ ለሚኖሩ ዜጎች የስራ እድልን በመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

ነገር ግን በቱሪስ መዳረሻዎች አካባቢ ያለው መሰረተ ልማት በተገቢው ባለመልማቱ ውጤታማ ሳይሆን ቆይቷል።

ይህንን በውል የተገነዘበው የመደመር እሳቤ ለቱሪዝም እምቅ አቅም ትኩረት በመስጠት የዘርፉን አሜኬላዎች በመንቀል ምቹ መደላድል ለመፍጠር በስፋት ለመስራት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል።

በዋናነት በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር እና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ዐይን የመግለጥ ስራ ተሰርቷል።

መንግሥት እንደ አብሪ ኮከብ በመሆን የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻዎች በቱሪዝም ዘርፉ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል መንገድ ጠርጓል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እውን የሆነው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮና ታሪካዊ ሀብቶች በማልማት ወደ ታላቅ የኢኮኖሚ ግብአትነት ለመቀየር በመንቀሳቀስ አስደናቂ ውጤት አምጥቷል።

የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆኑትና የስራውን ጥልቀትና ታላቅነት ሊመሰክሩ ለአገልግሎት ክፍት ሆነው የሚገኙት የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ የሸበሌ ሪዞርት፣ ደንቢ ኢኮ ሎጅ እና የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት ለአብነት የሚነሱ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቶቹ በቱሪዝም መስክ የታለመውን ከፍታ ለመቆናጠጥ ትልቅ አቅም መሆናቸው ታይቷል።

የገበታ ለትውልድ ሥራ ማሳያ የሆነው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በውብ ተፈጥሮ ላይ ተዘርግቶ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭና የኢኮኖሚውም ማገር ለማድረግ ወሳኝ ሀብት ነው፡፡

‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ማህበረሰብና ሀገርን በአንድ ላይ ለማበልጸግ የተተለመ የተከወነ ድንቅ ስራ ሲሆን፤ በቱሪስት መስህብ ሀብቱ ለሚታወቀው የአፋር ክልል ትልቅ አቅም የሚጨምር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

የቱሪዝም ፍሰትን ከመጨመር ባሻገር ታላላቅ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የሚያስተናግድና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥረው ፕሮጀክት፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ መሰራት የነበረበት የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ነበር፤ አሁን ስለዘገየን አንቆጭም።

ከ’ገበታ ለትውልድ’ ፕሮጀክቶች መካከል በሶማሌ ክልል በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሸበሌ ሪዞርት አንዱ ሲሆን፤ የቱሪዝም አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ የሚሰጥ ነው።

ሌላኛው የገበታ ለትውልድ ፍሬ የሆነው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ ላላት ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኝ የቱሪዝም ሀብት ተፈጥሮን መሰረት አድርጎ ማህበረሰባዊ እሴትን ለተቀረው አለም በማሳየት ክዋኔ ውስጥ ትልቅ እድል የያዘ ፕሮጀክት ነው፡፡

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት የየአካባቢዎቹን የማህበረሰብ አካላት ያሳተፈ መሆኑ ደግሞ ስራዎቹ በባለቤትነት ስሜት እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡

የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ የእድገትና የብልጽግና ታሪክ ውስጥ በደማቁ የሚጻፉ አንቀጾች ሆነው ለትውልድ ይቀመጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ማለም፣ ማቀድና በፍጥነት ማከናወን እንደሚቻል አሳይተዋል።

በመልካም ፍቃዱ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.