Logo
FBC
የምሁራን ዳር ሆኖ መመልከት ያሳስበኛል - መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምሁራን ዳር ሆኖ መመልከት ያሳስበኛል፤ አሁን ዳር የሚቆምበት ጊዜ አይደለም አሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ፡፡

መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ኮሚሽኑን ተቀላቅለው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያደረጓቸው ጉዞዎች አዲስና ተስፋ ሰጪ እይታ እንደጨመሩላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፣ በባህልና በጥቂት ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዎች ቢለያዩም፣ በደግነት፣ በአዛኝነት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ባላቸው አመለካከት በሚያስገርም ሁኔታ መመሳሰላቸው ትልቅ ተስፋ እንደሰጣቸው አውስተዋል፡፡

በአንጻሩ አብዛኛው የማሕበረሰብ ክፍል በሀገሪቱ የታዩት ችግሮች ምንጭ "ምሁራን እና የፖለቲካ ልሒቃን ናቸው" ብሎ እንደሚያምን እና መፍትሔውንም ከእነዚሁ አካላት እንደሚጠብቅ መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

"ሕዝቡ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እኛም ተካትተን መመካከር መቻላችን ትልቅ ዕድል ነው" እያለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የምሁራኑ ለዘብተኝነትና ዳር ሆኖ መመልከት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ዋና ኮሚሽነሩ በቁጭት ተናግረዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ሒደት በብዛት የምሁራንን ዕውቀትና ግብዓት የሚሻ ቢሆንም ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኛው ምሁር ዳር ሆኖ መመልከትን መምረጡን በማንሳት፣ "ያለን አንድ ሀገር በመሆኑ አሁን ዳር ቆሞ የመመልከቻ ጊዜ አይደለም" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህ ምክንያት አብነት አድርገው የጠቀሱት ኮሚሽኑ ሒደቱን ለመምራት የሚያስፈልጉ 192 አማካሪዎችን ፍለጋ ፈታኝ ጊዜ ማሳለፉን ነው፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻቸው ላይ በነፃነት መክረው ለመፍትሔው ቀጠሮ መያዛቸው ሒደቱ በራሱ ትልቅ አስተማሪና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ታሪካዊ ሒደት ስኬት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚገባውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቅድስት ዘውዱ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፦ https://youtube.com/watch?...

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.