Logo
Getu Temesgen
የቡድን-7 (G7) መሪዎች በፈረንሳይ በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ተወጥረዋል
#ethiopia | ​በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በጄኔቫ ሐይቅ ደቡባዊ ዳርቻ እየተካሄደ ባለው የዓለማችን ቁንጮ የበለጸጉ ሀገራት (G7) ጉባኤ ላይ የተገኙት መሪዎች፣ እያንዳንዳቸው የተለያየ የፖለቲካ አጀንዳና የቤት ሥራ ይዘው ቀርበዋል። አፍሪካም በአልሲሲ እና ሩቶ ተወክላለች።

​ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ (አሜሪካ)፦ በሀገራቸው ካለው ዝቅተኛ የሕዝብ ድጋፍና ከፊታቸው ከሚጠብቃቸው የምርጫ ፈተና ለማምለጥ፣ የኢራንን ጦርነትና ያስከተለውን የኢኮኖሚ ቀውስ መቋጨት ይፈልጋሉ። ከቴህራን ጋር የደረሱበት የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት መነሻ ቢሆንም፣ ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ግን ከሌሎች መሪዎች ጥያቄ እየቀረበባቸው ነው።

​ፕሬዚዳንት አማኑኤል ማክሮን (ፈረንሳይ)፦

የጉባኤው አስተናጋጅ ማክሮን፣ በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው ላይ በመሆናቸው በዓለም አቀፍ መድረክ ታሪካዊ አሻራ ጥለው ለማለፍ ይሻሉ። በሀገር ውስጥ ፖለቲካ እጃቸው ቢታሰርም፣ አውሮፓ "ስትራቴጂካዊ ራስን የመቻል" አቅም እንዲኖራት በንቃት እየወተወቱ ነው።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር (ብሪታንያ)፦

በሀገር ውስጥ ባለው የፖለቲካ ውጥረትና በቅርቡ በሚደረግ ድጋሚ ምርጫ የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ስለሚችል፣ ለብሪታንያ ሕዝብ አሁንም አስተማማኝ መሪ መሆናቸውን ለማሳየት በጉባኤው ላይ እየጣሩ ነው።

​ቻንስለር ፍሪድሪክ መርዝ (ጀርመን)፦

ከዚህ ቀደም የኢራንን ጦርነት በመንቀፋቸው ትራምፕ የአሜሪካን ወታደሮች ከጀርመን አስወጥተውባቸው ነበር። በትራምፕ ዘንድ መልካም ስም ለማግኘት ቁጥር 47 የተጻፈበትን የጀርመን እግር ኳስ ማሊያ በስጦታ በማበርከት ጉባኤውን ጀምረዋል።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ (ጣሊያን)፦

ከትራምፕ ጋር የነበራቸው የቅርብ ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በትራምፕ በበሸቀው የጣሊያን ሕዝብ ዘንድ የፖለቲካ ዕዳ ስለሆነባቸው፣ ራሳቸውን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለማራቅ እየሞከሩ ነው።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ (ካናዳ)፦

አሜሪካ መራሽ ባልሆነው ዓለም ውስጥ መካከለኛ ኃይል ያላቸው ሀገራት ስለሚኖራቸው ሚና ባቀረቡት አዲስ የፖለቲካ ዕይታ፣ በጉባኤው ላይ እንደ ትልቅ ነገር ታይቶላቸዋል።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካይቺ (ጃፓን)፦

በቅርቡ ባገኙት የምርጫ ድል ጠንካራ መሠረት ላይ ቢሆኑም፣ በኢራን ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋቱ በነዳጅ ላይ ጥገኝ ለሆነችው ጃፓን ትልቅ ፈተና በመሆኑ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ዋስትናን አስመልክቶ ለመወያየት ይሻሉ።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.