Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) በዓለም ዋንጫው ሀያሏን ስፔን ያለምንም ግብ (0-0) አቻ ያሰረችው ኬፕ ቨርዴ በፈጠረችው ታሪካዊ ክስተት የዓለምን ትኩረት መሳቧን ቀጥላለች። ይህን አስገራሚ ውጤት ተከትሎ፣ የቀድሞው የቶተንሃም እና የአውስትራሊያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ ለተጫዋቾቹ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል።

አሰልጣኙ በእንግሊዙ አይቲቪ (ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በሰጡት ትንታኔ "የስፖርት እና በተለይም የእግር ኳስ ታላቅነት ያለው በቁጥር በማይሰሉ እና በዓይን በማይታዩ ስሜቶች ውስጥ ነው" ብለዋል። "ዛሬ የኬፕ ቨርዴ ተጫዋቾች በምንም ተአምር እጅ ላለመስጠት በውስጣቸው የነበራቸው ወኔ እጅግ አስገራሚ ነበር" በማለት የቡድኑን የልብ ጥንካሬ አወድሰዋል።

በእግር ኳስ ትንታኔ ውስጥ የሚታየውን ክፍተት ሲያብራሩም "እኛ ጨዋታዎችን በወረቀት ላይ ስንተነትን ስፔን በቀላሉ ታሸንፋለች ብለን መደምደማችን አይቀርም፤ ነገር ግን እነዚያ የኬፕ ቨርዴ ተጫዋቾች በልባቸው ውስጥ ያዘሉትን ጥልቅ ስሜት እና ወኔ ከግምት ውስጥ አናስገባም" ብለዋል።

ፖስቴኮግሉ የዚህን የአቻ ውጤት ትርጉም ከሜዳ ውጪ ሲገልጹ "አሁን የዚህች አነስተኛ ሀገር ዜጎች 'እኛ ከኬፕ ቨርዴ ነን' ብለው በኩራት የሚናገሩበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል፤ ከዛሬ ጀምሮ መላው ዓለም ማንነታቸውን አውቆላቸዋል" በማለት ታሪካዊቷ ምሽት ለሀገሪቱ ያመጣችውን ትልቅ የገጽታ ግንባታ መስክረዋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.