Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የጋምቢያ ፕሬዝደንት አርሰናል ዋንጫ ማግኘቱን በማስመልከት በቤተመንግስታቸው ትልቅ ድግስ አደረጉ፡፡ የረጅም ጊዜ የአርሰናል ክለብ ደጋፊ የሆኑት የጋምቢያው ፕሬዝደንት አዳማ ባሮ በቤተመንግስታቸው ትልቅ ድግስ ማከናወናቸው ተሰማ፡፡ ትላንት እሁድ ጁን 14 ቀን 2026 በተደረገው በዚህ ድግስ ላይ የሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው የአርሰናል ደጋፊ ጋምቢያዊያን ተገኝተው ነበር፡፡

ፕሬዝደንቱ ባደረጉት ንግግር የሰሜን ለንደኑን ክለብ መደገፍ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ2000 መጀመሪያ መሆኑን ገልፀው ያኔ መኖሪያቸው እንግሊዝ ውስጥ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ፕሬዝደንት አዳማ ባሮ አርሰናል ዋንጫ ማግኘቱን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ የደስታ መልእክት ያስተላለፉት ወዲያው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳ የትላንቱ ይህ የቤተመንግስት ድግስ በአገሪቱ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ዘንድ ከፍተኛ ትችን አስከትሎባቸዋል፡፡ ‹‹ዩናይት ሙቭመንት ፎር ቼንጅ›› የተሰኘው ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ‹‹የመንግስትን ወንበር የእግርኳስ መመልከቻ ማእከል ማድረግ ተገቢ አይለም›› ሲል ወቅሷል፡፡ አገሪቱ በኢኮኖሚ ችግር፣ የምግብ ዋስትና ማጣትና የሀይል ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት እንዲህ አይነት ድግስ ማዘጋጀት ግድ የለሽነት ነው ሲሉም አክቲቪስቶች ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የጋምቢያ የአርሰናል ደጋፊዎች በበኩላቸው የፕሬዝደንቱን ድርጊት ደግፈው ተከራክረዋል፡፡ የደጋፊዎቹ ተወካዮች ለዜና አውታሮች በሰጡት መግለጫ ‹‹ድርጊቱ አገሪቱን በአለም አቀፍ እግር ኳስ አድናቂዎች ተርታ ያስቀመጠና ምንም ጉዳት የሌለው የግል ደስታ ጊዜ ነበር›› ብለዋል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.