Logo
Getu Temesgen
ሦስት ኢትዮጵያውያን የ2026ቱ የአፍሪካ ምርጥ 100 ሥራ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ
#ethiopia | በጃክ ማ ፋውንዴሽን እና በአሊባባ ፊላንትሮፒ አዘጋጅነት በሚካሄደው 'የአፍሪካ ቢዝነስ ጀግኖች' (ABH) የ2026 ውድድር ላይ ሦስት ኢትዮጵያውያን የቢዝነስ ሰዎች ከአፍሪካ ምርጥ 100 ሥራ ፈጣሪዎች መካከል መመረጣቸው ተገለጸ። ለዚህ ውድድር ከ54ቱም የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ24,000 በላይ አመልካቾች ተሳትፈዋል።

​ዘንድሮ ዕውቅና የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን የኢግል-ላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሱፍቃድ ጌታቸው አማረ፣ የቻፓ ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናኤል ኃይለማርያም፣ እንዲሁም የቱር ባዮቴክ (Thur Biotech) ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳምሶን ፈንታዬ ናቸው።

​ኤቢኤች (ABH) እንዳስታወቀው፣ እነዚህ ምርጥ 100 ሥራ ፈጣሪዎች ከ27 የአፍሪካ ሀገራት የተመረጡ ሲሆን፤ በግብርና፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጤና አጠባበቅ እና በኃይል ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው። የዘንድሮውን ስብጥር በመምራት ግብርና 21 በመቶውን ሲይዝ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ደግሞ በ12 በመቶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

​አቶ ብርሱፍቃድ የሚመሩት ኢግል-ላየን ሲስተም ቴክኖሎጂ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን፣ የክፍያ፣ የብድር እና የሐዋላ ሥርዓቶችን የሚያለማ የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሲሆን፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ማስተርካርድ እና ቪዛ ጋር አብሮ ይሰራል።

​በሌላ በኩል፣ አቶ ናኤል የሚመሩት ቻፓ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሆኑት የኦንላይን የክፍያ ሥርዓቶች አንዱ ሲሆን፣ የንግድ ተቋማት ኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችን በቀላሉ እንዲቀበሉ እና አፍሪካውያን የንግድ ተቋማትን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቶች ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል መሠረተ ልማት ያቀርባል።

ሦስተኛው ተወዳዳሪ አቶ ሳምሶን የሚመሩት ቱር ባዮቴክ ደግሞ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎችን በማምረት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሰራ የባዮቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።

​እነዚህ ምርጥ 100 ኩባንያዎች በ2025 እ.ኤ.አ. በጋራ 170 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማመንጨታቸውን፣ ከ6,200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እና 10 ሚሊዮን ለሚጠጉ ደንበኞች በመላው አፍሪካ አገልግሎት መስጠታቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። ይህ አኃዝ አፍሪካውያን ሥራ ፈጣሪዎች እያበረከቱት ያለውን የጎላ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ያሳያል።

​የተመረጡት ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉ ሲሆን፣ ዳኞች ቁጥራቸውን በማጣራት ወደ 20 ግማሽ ፍጻሜ ተወዳዳሪዎች ዝቅ ያደርጉታል። የተመረጡት ተወዳዳሪዎች በመጪው ነሐሴ ወር በናይሮቢ፣ ኬንያ የቢዝነስ ሥራቸውን በማቅረብ፣ በመጨረሻዎቹ 10 ምርጥ ሥራ ፈጣሪዎች ውስጥ ለመካተት እና የ1.5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ፈንድ ተቋዳሽ ለመሆን ይወዳደራሉ።

በያፌት ገ/ህይወት

Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
#getutemesgen #getu

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.