Logo
EBC
ዓለም በዝምታ ቢያዘግምም ኢትዮጵያ ምድርን እያከመች ነው!
********************

በዓለማችን ላይ አሳዛኝ እና ዐይን ያወጣ ኢፍትሐዊነት ቢኖር፣ ምድራችንን በበካይ ጋዝ እያፈኗት ያሉት ኃያላን ሀገራት ሲሆኑ፣ የጥፋታቸው ገፈት ቀማሽ ደግሞ ለብክለቱ ኢምንት የማያበረክቱ ደሃ ሀገራት መሆናቸው ነው።

አስቡት፤ አጠቃላይ የዓለማችንን የበካይ ጋዝ ልቀት ከ75 እስከ 80 በመቶ የሚያመነጩት ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው የቡድን 20 ሀገራት ናቸው።

በአንጻሩ፣ 54 ሀገራትን አቅፋ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አፍሪካ ለዚህ በካይ ጋዝ ያላት አስተዋፅኦ ከ3 እስከ 4 በመቶ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን ለችግሩ ያበረከቱት አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም በድርቅ፣ በጎርፍ እና በሙቀት መጨመር ግንባር ቀደም ሰለባ ሆነው ዘመናትን አሳልፈዋል።

የፈረሱ ስምምነቶች እና የወረቀት ላይ ቃላት

የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የሆኑት እነዚህ ኃያላን ሀገራት፣ ምድርን በካርቦን ጋዝ እያፈኗት መሆኑን አምነው፣ ልቀትን ለማስቀረትና ለችግሩ ሰለባ ለሆኑት ሀገራት ካሳ ለመክፈል በፓሪስ ታሪካዊ ስምምነት ፈረሙ።

ነገር ግን ዘመናት ተቆጠሩ፤ የወረቀት ላይ ቃላት ወደ ተግባር ሳይቀየሩ፣ ስምምነቶች የሚዲያ ፍጆታ ብቻ ሆነው ቀሩ። በኃያላኑ ቸልተኝነትና ቃል ማጠፍ ምክንያት ዓለማችን በድርቅ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በበረሃማነት መስፋፋት እና ባልተጠበቀ የአየር ጸባይ መዛባት ክፉኛ መታመሷን ቀጥላለች።

ከንግግር ወደ ተግባር፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አብዮት

ዓለም መፍትሔ አጥቶ በየስብሰባ አዳራሹ ሲባዝን፣ ቃሉን ሲያጥፍና ከንግግር ያለፈ አንዳች መፍትሔ ማምጣት ሲሳነው፣ ኢትዮጵያ ግን እጆቿን አጣጥፋ የኃያላኑን ምፅዋት አልጠበቀችም። ይልቁንም ተፈጥሮን እና አካባቢን ለማከም ቆርጣ በመነሳት ዓለምን ያስደመመ ተዓምራዊ የድል ትርክት መፃፍ ጀመረች።

ይህ ታሪካዊ የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዞ፣ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በይፋ ሲበሰር፣ ገና በዕለቱ 350 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል የህንድን የዓለም ክብረ-ወሰን በታላቅ ጀግንነት በመስበር ነበር የተጀመረው።

ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ በተረበሸችበት በ2012 ዓ.ም እንኳን፣ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሳይቆርጡ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ጽናታቸውን አሳይተዋል። በ2013 እና 2014 ዓ.ም ከ6 ነጥብ 8 እና 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በምድሪቱ ላይ ሲያርፉ፣ እንደ ሐሮማያ ሐይቅ ያሉ ጠፍተው የነበሩ የውሃ አካላት ዳግም ህያው ሆነዋል።

የድል መዳረሻዎቻችን በዚህ አላበቁም፤ በ2015 ዓ.ም ለምግብ ዋስትና የሚሆኑ የፍራፍሬ ተክሎች ላይ በማተኮር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተከሉ። በ2016 ዓ.ም ይህ አሃዝ ወደ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሲሻገር፣ በአንድ ጀንበር ብቻ ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የራሳችንን ክብረ-ወሰን ደግመን ሰበርን።

በመጨረሻም በ2017 ዓ.ም ከ8 ቢሊዮን በላይ ዐሻራዎችን በማኖር፣ በሰባት ዓመታት ጉዞ ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያ በዓለም የደን ልማት መዝገብ ላይ ወደር የማይገኝለት የልዕልና ስፍራ ተቀመጠች። በየዓመቱ ከ25 እስከ 35 ሚሊዮን ዜጎች በፈቃደኝነት የሚሳተፉበት ይህ ግዙፍ ንቅናቄ፣ ብሔራዊ አንድነትን ያጠናከረ የአረንጓዴ ማዕበል ሆኗል።

ይህ የ7 ዓመታት ጉዞ ያመጣው ሥነ-ምህዳራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተዓምር ቃላት ከሚገልጹት በላይ ነው። አስቀድሞ ወደ 3 በመቶ አሽቆልቁሎ የነበረው የሀገራችን የደን ሽፋን፣ በማይታመን ፍጥነት አድጎ 23 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል።

የተተከሉት ችግኞች ከ80 እስከ 85 በመቶ በሚደርስ የፅድቀት ምጣኔ ጸድቀው፣ በአማካይ 64 ሚሊዮን በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የሚያወጡትን በካይ ጋዝ ከከባቢ አየር ላይ በማጽዳት ዓለምን እየታደጉ ይገኛሉ።

መሬቱ ውሃን የመምጠጥ አቅሙ ከ16 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 68 ነጥብ 9 በመቶ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ፣ የተፋሰስ ልማቱ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦችን የዕድሜ ጣሪያ ቢያንስ በ50 ዓመታት እንዲራዘም አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር በተቋቋሙ ከ120 ሺህ በላይ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ሲፈጠር፤ ተፈጥሮ በማገገሟም የሀገራችን የቡና ወጪ ንግድ ከ230 ሺህ ቶን ወደ 475 ሺህ ቶን በማደግ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው።

በአጠቃላይ፣ ኃያላን ሀገራት ዛሬም ስለ አየር ንብረት ለውጥ ይነጋገራሉ፣ ስምምነት ያፈርሳሉ፣ ይከራከራሉ። ኢትዮጵያ ግን ንግግርን ወደ ተግባር ቀይራ፣ ቆስላ የነበረችውን ምድር በቢሊዮኖች አረንጓዴ ዐሻራ በተግባር እያከመች ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጥሮን ማዳን፣ ማክሮ-ኢኮኖሚን መገንባት እና ትውልድን ማሻገር መሆኑን አሃዞች አፍ አውጥተው እየመሰከሩ ነው።

የዓለምን የሥነ-ምህዳር ህመም ለመፈወስ እውነተኛው እና ህያው መድኃኒት ከኢትዮጵያ ተገኝቷል፤ ወደ 50 ቢሊዮን የሚያልመው የድል ትርክታችንም በብልጽግና ጎዳና ላይ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
#ethiopia #ebc #climatechange #greenlegacy #climateresilience

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.