Logo
FastMereja
የዓለም ዋንጫ እና አርሲ ሱዴ

​ሰዓቱ ምሽት ነው። አየሩ በአርሲ ሱዴ ቀዝቃዛ ንፋስ ታጅቦ በናፍቆት ይሞቃል። ዛሬ ዓለም በሜክሲኮ፣ አሜሪካ እና ካናዳ አስተናጋጅነት ለሚጀመረው የዓለም ዋንጫ በዝግጅት ላይ ሳለች፣ የእኔ ትውስታ ግን ከሃያ ዓመታት በፊት ወደ ነበረችው ኩላ ከተማ ያንገላታኛል።

​ያ ዘመን... ቴሌቪዥን በየቤቱ አልነበረም። የኢቲቪ እሁድ መዝናኛን ለመመልከት 50 ሳንቲም በእጅ ይዞ፣ በአንድ ትልቅ ስክሪን ፊት ለፊት ተሰባስቦ የመታየት ጣፋጭ ድካም የነበረበት ዘመን ነበር።

​ኩላ፣ ያቺ ትንሽዬ የወረዳ ከተማ፤ ከመኪና ወርደህ "የእከሌ ቤት የት ነው?" ብለህ ብትጠይቅ፣ ከመንገድ ዳር የሚጫወቱት ህፃናት "እኔ ላሳይህ!" ብለው የሚሻሙልህ፣ እያንዳንዱ ነዋሪ የአንዳችንን ማንነት የሚያውቅባት የሞቀች ከተማ። በዚያን ዘመን መብራት የሚባል ነገር አልነበረም። ጨለማውን የሚገፈው የአፍወርቅ እና የዲደዓ ቪዲዮ ቤቶች ጄኔሬተር ድምፅ ብቻ ነበር። ማታ ማታ የውጪ ፊልሞችን፣ በዓል ሲመጣም የኢቲቪን ፕሮግራሞች በነጻም እያስከፈሉ ያሳዩን ነበር። በተለይ የስቅለት ለሊት ቪዲዮ... ያ ድባብ ዛሬም ድረስ በአይኔ ይደቀናል።

የሩጫ ውድድር፣ ​ዓለም ዋንጫ እና አፍሪካ ዋንጫ ሲመጣ ደግሞ ከተማዋ ትናወጣለች! የአፍወርቅ እና የዲደዓ ቪዲዮ ቤቶች በሰው ተጨናንቀው የትንፋሽ እስራት ይፈጠራል። በስሜት መጮህ፣ በጎል መዝለል፣ በሽንፈት ማዘን... ያ ሁሉ ስሜት የጋራ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የተመልካቹ ብዛት ሲበዛ፣ የወረዳው መስተዳደር ጽ/ቤት ጄኔሬተር በማንሳት የራሱን በር ለህዝቡ ይከፍት ነበር። ያኔ፣ በአንድ ስክሪን ፊት የተሰባሰበው የኩላ ወጣት እና ታዳጊ፣ እንደ አንድ ቤተሰብ ነበር የሚሰማው።

​ዛሬ ግን ዘመኑ ተቀይሯል። ዓለም ዋንጫው በቴክኖሎጂው ዓለም ተውቦ፣ በእጅ ስልክ ስክሪን እየተመለከትን ነው። ርቀቶች ተሰርዘዋል።

​የዛሬይቱ ኩላ ምን ትመስል ይሆን? በየቪዲዮ ቤቱ ትከሻ ለትከሻ ተያይዘን የዓለም ዋንጫን ስንመለከት የነበርን ታዳጊዎች ዛሬ የት ደረስን? ምናልባት አንዳንዶቻችን በአሰላ፣ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ አንዳችን በውጪ አገር፣ አንዳችንም በኩላ የልጅነት ትዝታችንን እየናፈቅን በየስልካችን ስንመለከት ይሆን?

​ወይ ጊዜ! ያ የጋራ ትዝታ፣ ያ የተሰባሰበ ደስታ ዛሬም በልቤ ውስጥ የከበረ ቦታ አለው። ዛሬ ዓለም ዋንጫ ሲጀመር፣ ከሁሉም በላይ የናፈቀኝ ያ በኩላ ከተማ የነበረው የቡድን መንፈስ እና ያ የዋህ የልጅነት ደስታ ነው።

​የት ናችሁ የልጅነት ጓደኞቼ? ያ የኩላ ምሽት፣ ያ የዓለም ዋንጫ ወኔ ዛሬም ትዝ ይላችሁ ይሆን?

3 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.