Logo
FastMereja
ሚድሮክ የ80 ሚሊዮን ዶላር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራረመ
#fastmereja I ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) በኬንያ ናይሮቢ ከተማ የ80 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር የረጅም ጊዜ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱን የሚድሮክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ እና የIFC የአፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዚዳንት ኢትዮጲስ ተፈራ የፈረሙት ሲሆን፣ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በዋናነት ታዋቂውን ሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሽን ሆቴልን በዘመናዊ መልኩ ለማደስ እና በሸራተን ደረጃ አዲስ ተጨማሪ ሆቴል ለመገንባት ይውላል።

ይህ ከፍተኛ የፋይናንስ አጋርነት የሀገሪቱን የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም ዘርፍ ከማዘመን ባለፈ፣ ከ9,400 በላይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች እንደሚፈጥር ተገልጿል። አቶ ጀማል አሕመድ አጋርነቱ ቀጣይነት ላለው የሀገር ውስጥ ሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ሚና ሲያጎሉ፣ የIFC ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው ስምምነቱ የሚድሮክን የአገልግሎት ጥራት ለማሳደግ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ መመረጧን ተከትሎ ሚድሮክ ግዙፍ የሆቴል ማስፋፊያና የእድሳት ስራዎችን በከፍተኛ ፍጥነት እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል በሚሊኒየም አዳራሽ ቅጥር ግቢ የ"Moxy by Marriott"፣ በመሀመድያ የመኖሪያ መንደር የ"Four Points by Sheraton" እና በአፍሪካ ህብረት አጠገብ የ"Westin Addis" ሆቴሎች ግንባታ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።

በተጨማሪም በቅርቡ ግሩፑን የተቀላቀለው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ወደ "Autograph Collection by Marriott" ደረጃ የማደስ ስራው የተጀመረ ሲሆን፣ በባህርዳር፣ ጅማ፣ ሃዋሳ እና በላንጋኖ ሳቫና ሪዞርት ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ የሆቴል ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ንግድና ሆስፒታሊቲ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ይታወቃል።

4 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.