Logo
FBC
ሀገራዊ ምክክር እና ሀገር በቀል የእርቅ ዕሴቶች...

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲሁም ታሪካዊና መዋቅራዊ ቅሬታዎችን በውይይት ለመፍታት ታላቅ የብሔራዊ ምክክር ሂደት እያካሄደች ትገኛለች።

የዚህ ጉዞ ስኬት የሚወሰነው ከውጭ በሚቀዱ የፖለቲካ ቀመሮች ሳይሆን ማህበረሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ባቆያቸውና ከማንነቱ ጋር በተሳሰሩ የሰላምና የዕርቅ ዕሴቶች ላይ መመስረት ሲችል ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት የባህልና የማንነት ሕብረቀለም እንደመሆኗ መጠን እያንዳንዱ ማህበረሰብ ግጭቶችን የሚፈታበት፣ ፍትህን የሚያሰፍንበት እና የተናጋ ማህበራዊ ትስስርን የሚያድስበት የራሱ የሆነ ሀገር በቀል የዕርቅ ሥርዓት አለው።

ከእነዚህ ውድና ሕያው ማህበራዊ ዕሴቶች መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የደራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት “ደሃ” ተጠቃሽ ነው።

በደራሼ ማህበረሰብ ዘንድ “ደሃ” ወይም ሽምግልና ማለት እንዲሁ ግጭት ሲከሰት ብቻ የሚደረግ የጊዜያዊ ስምምነት ሂደት አይደለም። ይልቁንም ፍትህ የሚረጋገጥበት፣ የበደለ የሚጠየቅበት፣ የተበደለ የሚካስበትና ጠቅላላው ማህበራዊ ኑሮ ሕጋዊና ሞራላዊ እውቅና የሚያገኝበት ጠንካራ ዕሴት ነው።

ይህንን ሥርዓትን የሚመሩትና የሚያስፈጽሙት መሪዎች “ካዳያ” በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ መሪዎች የሚመረጡት በማህበረሰቡ ሕገ-ህሊና ውስጥ ባሉ ጥብቅ መስፈርቶች ሲሆን÷ የካዳያዎች የሥልጣን ዘመን ሁለት ዓመት ብቻ ነው።

ይህ የሚያሳየው በባህላዊ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ሽግግርና ለሌሎች ዕድል የመስጠት የዴሞክራሲ መርህ ቀድሞውኑ የነበረ መሆኑ ነው።

የደራሼ የዕርቅና የፍርድ ተግባር የሚከናወነው የማህበረሰቡ መረጃ የሚለዋወጥበት፣ ወጣቶችና አዛውንቶች የሚገናኙበት ዋነኛ ማዕከል በሆነው “ሞራ” በሚባል ጥላ በሚሰጡ ታላላቅ ዛፎች ሥር ድንጋዮች እንደ እርከን ከፍ ተደርገው በተዘጋጁ የሸንጎ ስፍራዎች ላይ ነው።

በደራሼ ባህል ሞራ ላይ ተከስሶ መቆም ትልቅ ማህበራዊ ውርደት ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ ማህበራዊ ሞራል ሰዎች ወንጀልና ጥፋት ከመስራታቸው በፊት ራሳቸውን እንዲገቱ ያደርጋቸዋል።

የደሃ የዳኝነት ሂደት ፍፁም ሰላማዊና ሥርዓታዊ ሲሆን÷ ተበዳዩ አቤቱታውን ካቀረበ በኋላ ተከሳሹ በምስክሮች ፊት እንዲቀርብ ይጠራል። ተከሳሹ የቀረበውን ጥሪ አሻፈረኝ ካለ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ማህበረሰባዊ ማዕቀብ ይጣልበታል።

በዳዩ በጥፋቱ ካመነ ደግሞ ሌላው አስደናቂ እሴት ይታያል፤ የካሳውን ክፍያ ጥፋተኛው ግለሰብ ብቻውን ሳይሆን የጎሳው አባል በሙሉ አዋጥቶ እንዲከፈል ይደረጋል።

ይህ እኔነትን ወደ እኛነት የሚቀይርና የአንዱ ጥፋት የሁሉንም ትኩረት እንዲስብ የሚያደርግ የጋራ ኃላፊነት መገለጫ ሲሆን÷ ዕርቁ የሚደመደመው ፍፁም ማህበራዊ ትስስርን በሚያድስ ታላቅ በዓል ነው።

ለዕርቁ ማሳረጊያ የሚሆን “ጨቃ” የተባለው ባህላዊ መጠጥና ምግብ የሚዘጋጀው የጎሳ አባላት እህል አዋጥተው በጋራ በመሥራት ነው።

በዕርቁ ቀን ከተበዳይና ከበዳይ ወገን የመጣው ምግብና መጠጥ አንድ ላይ ተደባልቆ በአንድ ማዕድ ይበላል። ፅዋቸውን ካነሱበት ሰዓት ጀምሮ ቁርሾው ሙሉ በሙሉ ተረስቶ ቀኑን በደስታ ያሳልፋሉ።

የደራሼ “ደሃ” ሥርዓት አሁን ኢትዮጵያ ለጀመረችው ብሔራዊ የምክክር ሂደት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ስልቶችንና ፍልስፍናዎችን ማበርከት ይችላል።

የዘመናዊው የፍትህ ሥርዓት ጥፋተኛውን መቅጣት ላይ ብቻ ሲያተኩር÷ የደሃ ሥርዓት ግን ትኩረቱ የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ላይ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩም እንደ ደራሼ ዕርቅ ሥርዓት ይቅርታንና ማህበራዊ ፈውስን ማምጣት ላይ ሊያተኩር ይገባል።

ዘመናዊነት ማለት የራስን መልካም እሴት መጣል ሳይሆን ባለው ሀገር በቀል እውቀት ላይ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ እሴት መጨመር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ሆነ መላው ሕዝብ እነዚህን ሕያው የሆኑ የባሕል ዕሴቶችን ለሀገራዊ መግባባት ሊጠቀምባቸው ይገባል።

የደራሼ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት የሚያስተምረን ታላቅ እውነት ቢኖር ችግሮቻችንን እኛው ራሳችን በራሳችን መድረክ በጥበብና በፍቅር መፍታት እንችላለን የሚለውን ዘላለማዊ ሀቅ ነው።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.